በሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት፣ በደቡብ ኮሪያና በዩናይትድ ስቴትስ አቻዎቻቸው መካከል ሊደረግ ለታቀደው ስብሰባና ውይይት ሰሜን ኮሪያ ዩናይትድ ስቴትስም ሆነች እርሣቸው ላይቀበሉት የሚችሉትን አንዳችም ቅድመ-ሁኔታ አለማስቀመጧን የደቡብ ኮሪያው መሪ ሙን ጄ-ኢን አስታወቁ።
የመሪዎቹ ስብሰባ ዓላማ የኮሪያ ልሣነ-ምድርን ከኒኩሌር የጦር መሣሪያ ነፃ የሆነ ቀጣና ለማድረግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መምከር ሲሆን የደቡቡ ፕሬዚዳንት ሙን ዛሬ ከንግድ መሪዎች ጋር ሶል ውስጥ ሲወያዩ ከአሜሪካ ወታደሮችን ከደቡብ ኮሪያ መውጣትን የመሳሰሉ ተቀባይነት ላይኖራቸው የሚችል ቅድመ-ሁኔታዎችን ፕዮንግያንግ እንዳላሰማች ተናግረዋል።
ሰሜን ኮሪያ እየጠየቀች ያለችው የደኅንነቷ ዋስትና እንዲሰጣትና ከምዕራቡ እየተሰነዘሩብኝ ነው የሙትላቸው የፀብና የጥላቻ ፖሊሲዎች እንዲወገዱ መሆኑን ሚስተር ሙን አመልክተዋል።
በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል የሚደረጉ ንግግሮች የፊታችን ሚያዝያ 19 ከሚደረገው የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ፤ የራሳቸውና የፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን ስብሰባ በኋላም ያለማቋረጥ እንደሚቀጥሉ ያስታወቁት ሙን ሰሜን ኮሪያ የኒኩሌር ጦር መሣሪያ መርኃግብሯን ሙሉ በሙሉ ለመሠረዝ ፍላጎት እያሳየች መሆኗን ገልፀዋል።
የዛሬ ሣምንት ዓርብ የሚካሄደው የሦስቱ መሪዎች ስብሰባ የሚደረገው ሰሜኑንና ደቡቡን በሚከፍለው በሃምሌ 1945 ዓ.ም. /በኢት. የዘ. አ./ በተፈረመው የኮሪያ ጦርነት ማብቂያ ውል መሠረት ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ እንዲሆን በተወሰነው ክልል ውስጥ በሚገኘው ፓንሙንጆም ቀበሌ ውስጥ እጅግ በተጠናከረ የፀጥታ ጥበቃ ሥር እንደሚሆን ታውቋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ