ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ በጦርነት ወቅት የጋራ መከላከያ እንዲኖራቸው ያደረጉትን ስምምነት ያወገዘው የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት፣ ለዩክሬን ጉዳት የማያደርሱ አቅርቦቶችን በገደብ ለመስጠት የሚከተለውን ፖሊሲ በድጋሚ እንደሚያጤነው አስታውቋል።
የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሐሙስ ዕለት አስተያየታቸውን የሰጡት፣ ጽህፈት ቤቱ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ፒዮንግያንግ ላይ ባደረጉት ጉባዔ የደረሱበትን ስምምነት በማውገዝ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ ነው።
ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው ስምምነቱ የደቡብ ኮሪያን ደህንነት አደጋ ላይ መጣሉን ገልጾ፣ ሲኦል ከሞስኮ ጋር ያላት ግንኙነት ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስጠንቅቋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ባለስልጣን፣ ሲኦል በምላሹ ዩክሬን የሩሲያን ወረራ መዋጋት የሚያስችላትን የጦር መሳሪያ የማቅረቡን ሀሳብ በድጋሚ እንደምታጤነው ተናግረዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፍ በሚገባ የታጠቀ ጦር ያላት እና የጦር መሳሪያዎችን በመላክ የምትታወቀው ደቡብ ኮሪያ ለዩክሬን ሰብዓዊ እርዳታ እና ሌሎች ድጋፎችን የምትሰጥ ሲሆን፣ በሞስኮ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ትደግፋለች።
ሆኖም በጦርነት ውስጥ ላሉ ሀገራት የጦር መሳሪያ ላለመስጠት በምትከተለው ፖሊሲ ምክንያት እስካሁን ለዩክሬን በቀጥታ የጦር መሳሪያ አልሰጠችም።
ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ በፒዮንግያንጉ ጉባዔ ላይ የፈጸሙት ስምምነት በጦርነት ጊዜ ሁለቱም ሀገሮች አፋጣኝ ወታደራዊ እርዳታ ለመስጠት ማንኛውንም መንገድ እንዲጠቀሙ የሚጠይቅ መሆኑን የሰሜን ኮሪያ የመንግስት መገኛኛ ብዙሃን ሐሙስ እለት ዘግበዋል።
መድረክ / ፎረም