በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን ሰገን ዙርያ ወረዳ ከሁከት ጋራ በተያያዘ ባለፈው ዓመት ነሐሴ 2016 ዓ.ም. የታሰሩት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ኡርማሌ ኡጋንዴ እንዲለቀቁ አንድ የቤተሰባቸው አባል ጠየቀ።
“አቶ ኡርማሌ የታሰሩት ጥቃቱን በተመለከተ በተለይም ስለተገደሉ ሰዎችና ስለወደመው ንብረት ለቪኦኤ አስተያየት በመስጠታቸው ነው”ሲሉ ወንድማቸው አቶ ማቲዮስ ኡጋንዴ ለአሜሪካ ድምፅ ተናገሩ።
አቶ ኡርማሌ አከባቢው ሰላማዊና የተረጋጋ እንዲኾን ከማድረግ ውጭ በየትኛውም ወንጀል ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ የላቸውም ፤ ይልቁንስ በወቅቱ በነበረው ኹከት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ሲያደርጉ ነበር ሲሉ አክለዋል።
የኮንሶ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሰሎሞን ካባይታ፣ “አቶ ኡርማሌ የታሰሩት በወንጀል ስለተጠረጠሩ እንጂ መግለጫ ስለሰጡ አይደለም” የታሰሩት ሲሉ ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
ምርመራ እየተደረገባቸው እንደኾነ ጠቅሰው ሰሞኑንም በሰገን ከተማ በተደረገ ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸውና ሁለቱ መቁሰላቸውን ገልጸዋል።
መድረክ / ፎረም