ማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚገኘው አንጋጫ ሆስፒታል የጤና ባለሞያዎች ትርፍ ሰዓት ክፍያ ስላልተከፈላቸው፣ በክልሉ ካምባታ ዞን አንጋጫ ወረዳ የሚገኘውና በአካባቢው ለሚገኙ 2 መቶ ሺሕ ለሚኾኑ ነዋሪዎች አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው አንጋጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት ተቋረጠ።
አገልግሎቱ የተቋረጠው ሃኪሞቹን ጨምሮ 80 የሚኾኑ፣ የጤና ባለሞያዎች ለስድስት ወራት የሠሩበት የትርፍ ሰዓት ክፍያ ስላልተከፈላቸው መኾኑን ተናግረዋል። የሆስፒታሉ አገልግሎት የተቋረጠው ካለፈው ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀመሮ ሲኾን ተገልጋይ የኅብረተሰብ ክፍሎች መቸገራቸውን ተናግረዋል።
የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሰማ አበራ፣ ለሠራተኞቹ የስድስት ወር ክፍያ አለመፈጸሙን እና ባለሞያዎቹም ሥራ ማቋረጣቸውን አረጋግጠዋል።
የካምባታ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ ዶክተር ራማሮ አቦ፣ ችግሩን ለመፍታት ለሠራተኞቹ ጥሪ ቢያቀርቡም ሠራተኞቹን ማግኘት እንዳልተቻለ ገልጸዋል። የተቋሙን ቁልፍ ይዘው ጠፍተዋል ያሏቸው ባለሞያዎም በሕግ እንደሚጠየቁ ተናግረዋል። ከሌሎች ጤና ጣቢያዎች ባለሞያዎች በማስመጣት ድንገተኛ ህክምና ለመስጠት እየተሞከረ መኾኑንም አክለዋል።
መድረክ / ፎረም