በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ኮሬ ዞን፣ ጎርካ ወረዳ፣ ሻሮ ቀበሌ፣ አራት አርሶ አደሮች፣ ትላንት መስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም በታጣቂዎች መገደላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦችና የአካባቢው አስተዳደር አስታወቀ። ታጣቂዎቹ አርሶ አደሮቹን የገደሏቸው፣ ከብቶቻቸውን ሲያግዱ ከነበሩበት ቦታ አግተው ከወሰዷቸው እና የማስለቀቂያ ገንዘብ ከተቀበሉ በኋላ መሆኑን ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል። የኮሬ ዞን ሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተፈራ ቦንዶራ፣ ጥቃቱን የፈፀመው በአከባቢው ታጠቆ የሚንቀሳቀሰው የፌዴራል መንግሥቱ ሸኔ በማለት የሚጠራው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ነው፤ ሲሉ ወንጅለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ የፀጥታ እና አሰተዳደር ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ጂኦ በበኩላቸው፣ በአከባቢው ያለው ጥምር የፀጥታ ኃይል፣ በታጣቂዎቹ ላይ እርምጃ እየወሰደ ነው ብለዋል።
መድረክ / ፎረም