የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የውጭ ምንዛሬ ተመኑ ገበያ መር እንዲኾን መወሰኑን ተከትሎ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል “ያለአግባብ ዋጋ ጨምረዋል፤ ምርትም ደብቀዋል” የተባሉ 297 ነጋዴዎች መታሰራቸውንና ከ3ሺሕ300 በላይ የንግድ ተቋማት መታሸጋቸውን፣ የክልሉ የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
ይኹንና፣ ታሽገዋል ከተባሉ የንግድ ተቋማት ውስጥ ሳይቀር፣ ሸቀጦችን የመሰወርና የማሸሸ ድርጊት እየተፈጸመ መኾኑን ለአሜሪካ ድምፅ የገለጹ ሸማቾች በበኩላቸው፣ እየተወሰደ ነው የተባለው ርምጃም መፍትሔ ያስገኛል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡
አስተያየታቸውን ለአሜሪካ ድምፅ የሰጡ ነጋዴዎችም፣ ከምንዛሬ ተመን ፖሊሲ ለውጥ ጋራ በተገናኘ የእስር እና ሱቆችን የማሸግ ርምጃው “ተገቢነት የለውም፤” ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህር ደግሞ፣ ነጋዴዎችን የማሰር ርምጃው የነጻ ገበያ የኢኮኖሚ ሥርዓትን የሚፃረርና ውጤቱም ጊዜያዊ መኾኑን ገልጸው ተችተዋል፡፡ ዘላቂ መፍትሔውም፥ “ምርታማነትን በማሳደግ የአቅርቦት እና ፍላጎት ክፍተቱን ማቀራረብ ነው፤” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
መድረክ / ፎረም