ደቡብ አፍሪካ አንድ የልዑካን ቡድን ወደ አሜሪካ በመላክ፣ በዲፕሎማሲ፣ ንግድ እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንደምትሻ ፕሬዝደንት ሰሪል ራማፎሳ አስታውቀዋል።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው የቡድን 20 ዓባል ሀገራት ጉባኤ ጎን የተናገሩት ራማፎሳ፣ ወደ አሜሪካ የሚላከው ቡድን በርካታ አለመግባባቶችን ለማስወገድ እንደሚወያይ አስታውቀዋል። በደቡብ አፍሪካው ጉባኤ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አልተገኙም።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ደቡብ አፍሪካ ከነጮች ላይ መሬት ልትነጥቅ ነው በሚል የሀገሪቱን መንግሥት ተችተው የገንዘብ ድጋፍ አናቆማለን ብለው ነበር። ትችቱ የመጣው ራሞፎሳ መንግሥት በሚወርሰው ንብረት ምትክ እንደ ሁኔታው ካሳ ላይከፍል እንደሚችል የሚያመለክተውን ሕግ ባለፈው ወር በፊርማ ማጽደቃቸውን ተከትሎ ነው።
“ወደ አሜሪካ የምንሄደው ምክንያት ለመደርደር ሳይሆን፣ በበርካታ መስኮች ከአሜሪካ ጋራ ትርጉም ያለው ስምምነት ለማድረግ ነው” ብለዋል ራማፎሳ። ሕጉ አስፈላጊ የሆነው ሕዳጣን የሆኑት ነጮች የዘር መድልኦ ከተወገደ ከ30 ዓመታት በኋላም አብዛኛውን የእርሻ መሬት ይዘው በመቆየታቸውና እኩልነትን ማስፈን አስፈላጊ በመኾኑ እንደሆነ ተመልክቷል።
መድረክ / ፎረም