በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም ዋንጫ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ጥቂት ሰዓታት ቀርተውታል


የባፋና ባፋና ደጋፊዎች
የባፋና ባፋና ደጋፊዎች

በከፍተኛ ደረጃ ደማቅና አስገራሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል

ደቡብ አፍሪቃ በነገው ዕለት በአህጉሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ለመጀመር እየተዘጋጀች ባለችበት ባሁኑ የመጨረሻ ሰዓት ላይ፥ ዋና ከተማዋ ጆሀንስበርግ፥ እንግዶቿን በሙዚቃና ልዩ ልዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞች እያዝናናች ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙዚቀኞች፥ ደናሾችና አርቲስቶችም በነገው ዕለት የመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ የሚያቀርቧቸውን ትርዒቶች የመጨረሻ ልምምድ እያጠናቀቁ ነው።

በባህላዊ ልብሶች ያሸበረቁ ዘማሪዎችና ጨፋሪዎች በሙዚቃ ባንድ ታጅበው በጆሐንስበርግ ሶከር ሲቲ ስታድዮም የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሲያደርጉ ነው የሚደመጡት። በዚያ አካባቢ የሚያልፉ መኪኖችም ድጋፋቸውን ለማሳየት፥ ጡሩንባቸውን ያጮሃሉ።

የደቡብ አፍሪካ ደጋፊዎች
የደቡብ አፍሪካ ደጋፊዎች

« ከወዲሁ እየተሰማኝ ነው። በዓለሙ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ተደስቼአለሁ » ብሏል መንገድ ላይ ከወጡት ደጋፊዎች መካከል የሚገኘው አንዱ የኳስ አፍቃሪ።

በነገው በከፍተኛ ደረጃ ደማቅና አስገራሚ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው የዓለም ዋንጫ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ይቀርባሉ የሚባሉት ከ 1, 500 በላይ የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ አርቲስቶች ቢሆኑም፥ ትርዒቶቹን አፍሪቃዊ ለማድረግ እንደሚጥሩ አዘጋጆቹ ቃል ገብተዋል።

የባህል ሚኒስትሩ ሉሉ ዚንግዋና የመክፈቻው ሥነ በዓል፥ በመጪው ሐሙስ የዓለም አቀፍና አፍሪቃውያን አርቲስቶች በሚካፈሉበት የሙዚቃ ኰንሰርት እንደሚቀጥል አውስተዋል።

« አፍሪቃዊ ባህልና ቅርስ የሚንፀባረቅበት ትርዒት ይሆናል ብለን እናምናለን። የኰንሰርቱን ድግስ ሶዌቶ በሚገኘው የኦርላንዶ ስታድዩም እና ትልቁን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ለመጀመር ዝግጁ ነን » ብለው አክለዋል የባህል ሚኒስትሩ።

አዘጋጆቹ እንደሚሉት፥ እንደ ሙዚቀኞች ህዩ ማሳኬላ, ፌሚ ኩቲ, ካሌድ, ኦሲቢሳ, አር ኬሊ እና የሶዌቶ መንፈሳዊ ዘማሪያን ያሉቱ በነገው ዕለት አስተናጋጅ ደቡብ አፍሪቃና ሜክሲኰ የመክፈቻውን ግጥሚያ ከማድረጋቸው በፊት ይሆናል ትርዒቶቻቸውን የሚያቀርቡት።

የፈረንሳይና ዑራጓይ ብሄራዊ ቡድኖችም በነገው ዕለት ማታ ይሆናል የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን የሚያደርጉት።

በሌላ በኩል ደግሞ፥ ትላንት ረቡዕ የንግድ መናኸሪያዋ ከተማ ጆሐንስበርግ ሳንድተን ወረዳ፥ ለብሄራዊ ቡድናቸው ለባፋና ባፋና ድጋፉን ለመግለጽ በወጣ እጅግ ብዙ ቁጥርባለው ሕዝብ ተሽመድምዳ መዋሏ ተዘግቧል።

በደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫን ግጥሚያዎች በሚያስተናግዱት ዘጠኙም ከተሞች፥ የመዝናኛ ፓርኰች ተዘጋጅተዋል። ቡድኖች በግላቸውና ነጋዴዎችም፥ የየራሳቸውን ፈንጠዝያ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል። የፉት ቦል ጭፈራው በየስፍራው ለአንድ ወር ሙሉና አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃ ዋንጫውን ካስቀረችም ከዚያ በኋላ ለረዥም ጊዜ ሊቀጥል ይችላል። ላሁኑ ግን ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ የስፖርቱ አፍቃሪዎችና ጐብኚዎች ነገ የውድድሮቹን መጀመር በታላቅ ጉጉት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

እነዚህን በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የእግር ኳስ አፍቃሪዎችና ጐብኚዎች ደህንነት ለመጠበቅም አገሪቱ ብዙ ዝግጅቶችን አድርጋለች። በተለይ ሁለት የጋዜጠኛ ቡድኖች ከመክፈቻው በዓል ዕለት በሌቦች ከተዘረፉ በኋላ፥ ዛሬ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የመንግሥቱ ቃል አቀባይ ቴምባ ማሴኮ በዛሬው መግለጫቸው፥ ለሁሉም ማለትም ለዜጐቻቸውና ለእንግዶች ተማጽኖ አቅርበዋል።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች በልምምድ ላይ
የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች በልምምድ ላይ

ደቡብ አፍሪቃ በጠቅላላው በአገሪቱ 190, 000 ፖሊሶች ያሏት ሲሆን፥ በዓለም ዋንጫ ውድድሮች ወቅት ያሰማራቻቸው፥ 40, 000 የሚሆኑትን ብቻ ነው። በውድድሮቹ የሚሳተፉ የ 32ቱ ቡድኖች አገሮች ድጋፍ ግን አላቸው። ማለትም የተሳታፊ አገሮቹ መንግሥታት የየራሳቸው የፖሊስ ልዑካን አሏቸው። ብዙም ባይሆኑ እንደየአገሮቹ አቅም ካነስተኛ እስከ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ፖሊሶች መድበዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ብዛት ያላቸውን ፖሊሶች ከተጫዋቾቹ ጋር ልካለች።

እንግዲህ ቀሪዎቹ 150, 000 የደቡብ አፍሪቃ ፖሊሶች በተጨማሪ በቀን 24 ሰዓት መደበኛውን የዕለት ተለት ሥራቸውን ያከናውናሉ ማለት ነው።

በፖሊስ መግለጫ መሠረት ትላንት በፖርቱጋል ጋዜጠኞች ላይ በታጣቂ ወሮበሎች ከደረሰው ዝርፊያ ጋር በተያያዘ የሚጠረጠሩ ሦስት ሰዎች ተይዘውታሥረዋል። ሌቦቹ የሆቴል ክፍሎቻቸውን ሰብረው ገብተው ፓስፖርቶቻቸውን ገንዘብና የፊልም ማንሻ ካሜራዎቻቸውን እንደወሰዱባቸው ተናግረዋል። የቻይና መንግሥታዊው ሚዲያም፥ አራት ጋዜጠኞቹ ወደ ጆሐንስበርግ በመጓዝ ላይ በነበሩበት ወቅት ወሮበሎች አስቁመው በመሣሪያ በማስፈራራት እንደዘረፏቸው ዘግቧል።

በዓለም ከፍተኛ ወንጀል ይፈጸምባታል በምትባለው በደቡብ አፍሪቃ በየቀኑ ባማካይ 50 ግድያዎች ይመዘገባሉ። በመሆኑም የዓለም ዋንጫውን ለሚያዘጋጁ ባለሥልጣናት ከፍተኛው የራስ ምታት እንደሚሆንባቸው ይገመታል።

XS
SM
MD
LG