በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደቡብ አፍሪካ የእስራኤልን ፍልስጤማውያን አያያዝ ከአፓርታይድ ዘመን ጋር አነጻጸረች


ፎቶ ፋይል፦ ዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት ዘ ሄግ፣ ኔዘርላንድስ
ፎቶ ፋይል፦ ዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት ዘ ሄግ፣ ኔዘርላንድስ

ደቡብ አፍሪካ ዛሬ ማክሰኞ በመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የፍትህ ችሎት ላይ ባቀረበችው ሪፖርት ‘እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ በፈጸመችው የአፓርታይድ መሰል አያያዟ ተጠያቂ ናት’ ስትል ወነጅላለች። የፍልስጤማውያንን መሬት የያዘችበት እርምጃዋም ከአለም አቀፍ ድንጋጌዎች አንጻር "በመሠረቱ ህገ-ወጥ" ነው ብላለች።

ከአለም አቀፉ የፍትህ ችሎት ፊት የቀረቡት የደቡብ አፍሪካ ተወካዮች አሳሪ ያልሆነ ምክረ ሃሳብ ለመጠየቅ ጠቅላላ ጉባኤው በጠራው የችሎቱ ሁለተኛ ቀን ውሎ ላይ ባሰሙት ንግግር እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው ግዛቶች በምታራምደው ፖሊሲ ህጋዊነት ዙሪያ ላይም አስተያየት ሰጥተዋል። “የአፓርታይድ አስከፊና አስጸያፊ ድርጊቶች ተፈጽመው በተገኙበት ሥፍራ ሁሉ ደቡብ አፍሪካ የማጋለጥ እና በአስቸኳይም እንዲወገድ የማድረግ የገዛ ሕዝቧም ሆነ የአለም ማህበረሰብ ልዩ ግዴታ አለባት” ሲሉ በኔዘርላንድስ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ቩሲሙዚ ማዶንስላ 15 አባላት ላሉት የዓለም አቀፉ የዳኞች ቡድን ተናግረዋል።

እስራኤል በበኩሏ የደቡብ አፍሪቃን ‘የአፓርታይድ” ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች። ለወትሮው የመንግስታቱን ድርጅት እና የአለም አቀፉን ችሎት ኢ-ፍትሃዊ እና አድሏዊ አድርጋ የምትመለከተው እስራኤል በችሎቱ ውሎ ግን መግለጫ ከመስጠት ተቆጥባለች።

ይሁንና እስራኤል ባለፈው ዓመት በጽሁፍ ባቀረበችው መግለጫ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ያቀረባቸውን ጥያቄዎች ‘በጭፍን ጥላቻ የተሞሉ እና የእስራኤልን ዜጎቿን ከጥቃት የመከላከል መብት እና ግዴታ መቀበል የተሳናቸው ናቸው’ ስትል ተችታለች። አያይዛም “ለእስራኤል የደህንነት ስጋቶች እውቅና ለመስጠትም ሆነ በእስራኤል እና በፍልስጤም የግዛት ድንበሮች፣ እንዲሁም በጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚደረሱ ስምምነቶች እና ሰፈራን ጨምሮ ሁለቱን አገሮች በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ የሚካሄዱ ድርድሮች እና ስምምነቶች እልባት በማስገኘት ረገድ የረዳ አይደለም” ብላለች።

እስራኤል 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጤማውያን እንደሚኖሩ በሚገመትበት የዌስት ባንክ ዙሪያ አብዛኛዎቹ ሙሉ በሙሉ ከተገነቡ ትናንሽ ከተሞች እና የከተሞች ዳርቻዎች የሚቆጠሩ ከ500, 000 በላይ አይሁዳውያን ሰፋሪዎች የሚኖሩባቸው መንደሮችን ማቋቋሟ ይታወቃል። ምስራቃዊ እየሩሳሌምን ከግዛቷ ያዋሃደችው እስራኤል ከተማይቱን በሙሉም የመንግስቷ ዋና መቀመጫ አድርጋ ታያለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አለም አቀፉ ችሎት ጉዳዩ አስመልክቶ የሚሰጠው የመጨረሻ ብይን ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል ቢታመንም፤ እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ባለው ወታደራዊ ዘመቻዋ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን የሞት፣ የአካባቢ ውድመት እና ብሎም ማንኛውንም የዘር ማጥፋት ወንጀል ለማስቀረት የምትችለውን ሁሉ ታደርግ ዘንድ የመጀመሪያ ትዕዛዙን አስተላልፏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG