በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ ኦሞ እና ደራሼ ልዩ ወረዳ ግጭት 22 ተጠርጣሪዎችን መያዙን ፖሊስ ገለጸ


በደቡብ ኦሞ እና ደራሼ ልዩ ወረዳ ግጭት 22 ተጠርጣሪዎችን መያዙን ፖሊስ ገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:02 0:00

በደቡብ ኦሞ እና ደራሼ ልዩ ወረዳ ግጭት 22 ተጠርጣሪዎችን መያዙን ፖሊስ ገለጸ

በደቡብ ኦሞ ዞንና በደራሼ ልዩ ወረዳ፣ ሁከት በመፍጠር እና ሰው በመግደል ወንጀል የተጠረጠሩ 22 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን፣ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ግጭት በተፈጠረባቸው በእነዚኽ ሁለት አካባቢዎች፣ በድምሩ 13 ሰዎች መገደላቸውንና ከ10 በላይ መቁሰላቸውን፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ዓለማየሁ ማሞ፣ ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።

የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች፣ አሁን ወደ መደበኛ እና ሰላማዊ እንቅስቃሴ በመመለስ ላይ እንደኾኑና የወንጀል ተጠርጣሪ ናቸው የተባሉ ግለሰቦች እየታሰሩ መኾኑን ተናግረዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን ሳላማጎ ወረዳ፣ በሰዎች ግድያ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፣ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ዓለማየሁ ማሞ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ፣ ሰሞኑን፥ በደቡብ ኦሞ ዞን ሳላማጎ ወረዳ ሐና ከተማ፣ በቦዲ እና በዲሜ ጎሣዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት፣ 11 ሰዎች መገደላቸውን አስታውሰዋል።

የአሜሪካ ድምፅ ከአነጋገራቸው የሐና ከተማ ነዋሪዎች ውስጥ፣ ስማቸው እና ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን አስተያየት ሰጪዎች፣ በወረዳው አንጻራዊ ሲሉ የገለጹት ሰላም ስለመስፈኑ፣ በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

እስከ አሁን ድረስ፣ 15 ተጠርጣሪዎች ስለመያዛቸው፣ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተገለጸውን አስመልክቶ እኚሁ አስተያየት ሰጪ ሲናገሩ፣ “ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በመንግሥት የተጠረጠሩ ሰዎች ከሁለቱም ወገን ተይዘዋል፤” ብለዋል፡፡

የ11 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የሁለቱ ጎሣዎች ግጭት ሲፈጠር፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ሚና እና አያያዝ ምን እንደነበር ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጥያቄ ቀርቧል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ ጋቶ ቀበሌ፣ ለሁለት ሰዎች ሞት እና ለአምስት ሰዎች መቁሰል ምክንያት ከኾነው ግጭትም ጋራ በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

የደራሼ ልዩ ወረዳ ጋቶ ቀበሌ ነዋሪ በበኩላቸው በአካባቢው የመንግሥት የፀጥታ ኃይል በመግባታቸዉ መረጋጋቱን ገልፀው መያዝ ይገባቸው ነበር ያሏቸው ተጠርጣሪዎች ግን እንዳልተያዙ ገልፀዋል።

በደራሼ ልዩ ወረዳ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር፣ ከሌላ ብሔረሰብ ጋራ የሚገናኝ አለመኾኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፣ አሁን አካባቢው ወደ መደበኛ ሰላም መመለሱን ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል የጸጥታ ኹኔታ፣ “የራሱ ባሕርይ” እንዳለው የገለጹት ኮሚሽነር ዓለማየሁ፣ አሁን ክልሉ ሰላማዊ ነው፤ ሲሉ ተናግረዋል። ኮሚሽነሩ፣ አልፎ አልፎ የሚከሠቱ ናቸው፤ ያሏቸው የጸጥታ ችግሮች ግን፣ ልዩ ልዩ መልክ ያላቸው ስለመኾናቸው አስረድተዋል።

በሁለቱ አካባቢዎች በአጠቃላይ ከታሰሩ 22 ሰዎች ውስጥ፣ ሰባቱ በደራሼ ልዩ ወረዳ ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲኾኑ፣ ከዚኹ ድርጊት ጋራ በተገናኘ ተሰውረዋል ያላቸውንም ለመያዝ፣ መንግሥት ክትትል እያደረገ መኾኑን ኮሚሽነሩ ለቪኦኤ ገልጸዋል።

/ሙሉ ዘገባው ከፋይሉ ጋራ ተያይዟል/

XS
SM
MD
LG