በድጋሚ የታደሰ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር ሀገራቸው ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደምታቋርጥ በመገናኛ ብዙሃን የተሰራጨውን ዘገባ አስተባብለዋል።
ዜናው የተሰማው አብዱልቃድር ኢድሪስ በመባል የሚታወቁት የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ እና የሶማሊያ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር እንደሆኑ የተጠቀሱት ኤርትራዊ ባለስልጣን በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተደረሰው የአንካራ ስምምነት እንዳሳሰባቸው ቢቢሲ ሶማሌ መዘገቡን ተከትሎ ነው።
የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል በተጠቀሰው ስም የሚጠሩ ባለስልጣንም ሆነ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተባለው ቢሮ አለመኖሩን ለቪኦኤ አፍሪካ ቀንድ አስታውቀዋል። .
ቢቢሲ ሶማሊኛ ባለሥልጣኑ “ኢትዮጵያ የምትሻው የባሕር ኅይል መሠረት እንጂ የባሕር አቅርቦት አይደለም” ሲሉ መናገራቸውን ጠቅሷል።
“ሶማሊያ ለኢትዮጵያ የባሕር መሠረት የምትሰጥ ከሆነ፣ ኤርትራ ከሶማሊያ ጋራ ያላትን ግንኙነት እንደገና ታጤናለች” ሲሉ አብዱልቃድር ኢድሪስ የተባሉት ባለሥልጣን መናገራቸውን ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።
የኤርትራው ማስታወቂያ ምኒስትር የማነ ገ/መስቀል ዘገባውን “ሃስት” ሲሉ ገልጸውታል።
“አብዱልቃድር ኢድሪስ የሚባል ባለሥልጣን በኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የለም። በኤርትራ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ‘የአፍሪካና ሶማሊያ ጉዳዮች አማካሪ፣ ተብሎ የሚጠራ መዋቅር በሚኒስቴር መ/ቤቱ የለም” ሲሉ የማነ ገብረ መስቀል ለቪኦኤ አፍሪካ ቀንድ አስታውቀዋል።
“ኤርትራ ከሶማሊያ ጋራ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ ዝታ አታውቅም” ሲሉም አክለዋል ምኒስትሩ።
የቪኦኤ አፍሪካ ቀንድ የቢቢሲን አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
መድረክ / ፎረም