ፍልሰተኞችን የያዙ ሁለት ጀልባዎች በማዳጋስካር ባህር ዳርቻ ተገልብጠው 22 ሶማሊያውያን ህይወታቸው ማለፉን የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስትር ዳውድ አዌይስ አስታወቁ።
የማዳጋስካር የወደብ፣ የባህር እና የወንዞች ባለሥልጣን አደጋውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ጀልባዎቹ ከሶማሊያ ተነስተው፣ ወደፈረንሳይ የህንድ ውቅያኖስ ግዛት ማዮት ጉዞ የጀመሩት ጥቅምት 23 ቀን ነበር።
ሆኖም ቅዳሜ ኅዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም ፣ ዓሣ አጥማጆች የመጀመሪያውን ጀልባ በኖሲ ኢራንጃ አቅራቢያ ባሕሩ ላይ በንፋስ እና በባሕሩ እንቅስቃሴ እየተገፋ ሲንሳፈፍ ማግኘታቸውን የወደቡ ባለሥልጣናት አመልክተዋል። ጀልባው ላይ ተሳፍረው ከነበሩት ሰዎች ውስጥ 10 ወንዶችን እና 15 ሴቶችን ጨምሮ በድምሩ የ25 ሰዎችን ህይወት ማዳን ቢቻልም፣ የሰባት ተሳፋሪዎች ህይወት ግን ማለፉን ባለሥልጣኑ አስታውቀዋል።
38 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረው ሁለተኛው ጀልባ ማዳጋስካር ወደብ ላይ መድረስ መቻሉን ያመለከተው መስሪያ ቤቱ፣ 23 ሰዎችን በህይወት ማትረፍ መቻሉን ቢያስታውቅም፣ ምን ያክል ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ግን አልገለጸም።
የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስትር አዌይስ በበኩላቸው ከማዳጋስካር አቻቸው እንዳገኙ የገለጹትን መረጃ ጠቅሰው፣ እስካሁን 22 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ መረጋገጡን ተናግረዋል።
"በጀልባዎቹ ላይ ወደ 70 የሚጠጉ ሶማሊያውያን ነበሩ። ከነሱ ውስጥ 22ቱ ህይወታቸው አልፏል" ያሉት አዌይስ፣ አንደኛው ጀልባ 38 ሌላኛው ጀልባ 32 ፍልሰተኞችን አሳፍሮ እንደነበር አመልክተዋል።
ባለፉት አሰርት ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከፍ ያለ የኑሮ ደረጃ ወዳላት እና የፈረንሳይ የድጎማ ሥርዓትም ተጠቃሚ ወደሆነቸው ወደማዮት ባሕር አቋርጠው ለመግባት መሞከራቸው ተመልክቷል፡፡
መድረክ / ፎረም