በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊላንድ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ አሸነፉ


የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው መሐመድ አብዱላሂ ኢሮ
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው መሐመድ አብዱላሂ ኢሮ

በሶማሊላንድ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው መሐመድ አብዱላሂ ኢሮ ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ አብዲን ማሸነፋቸውን የምርጫ ኮሚሽኑ ዛሬ ማክሰኞ አስታወቀ፡፡

ገለልተኛ ታዛቢዎች ምርጫውን "ሰላማዊ "ሲሉ ገልጸውታል፡፡ የብሔራዊ ፓርቲው የዋዳኒ ፕሬዚደንታዊ እጩ አብዲራህማን መሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ) 63 ነጥብ 92 ከመቶውን የመራጭ ድምጽ ያገኙ ሲሆን ፕሬዚደንት ቢሂ 34 ነጥብ 81 ከመቶ፡ ሦስተኛው እጩ 0 ነጥብ 74 ከመቶውን ማግኘታቸውን የሶማሊላንድ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሴ ሀሰን ዩሱፍ ሐርጌሳ ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡

የ69 ዓመቱ ኢሮ ለአምስት ዓመት ሶማሊላንድን ሊመሩ እ አ አ ታሕሳስ 13 ቀን ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ፡፡

ብሐራዊ የምርጫ ኮሚሽኑ የምርጫውን ውጤት እንዲያጸድቅ ለከፍተኛ ፍርድ ቤቱ እንደሚያቀርበው ተመልክቷል፡፡

የሶማሊላንድ ምርጫ እአአ በ2022 ዓም ሊካሂድ ታቅዶ የነበረ ሲሆን በፖለቲካ ልዩነቶች የተነሳ እስካሁን ዘግይቷል፡፡

እአአ በ2017 በተካሄደው በቀደመው ምርጫ የዋዳኒ ፓርቲውን መሪ አሸንፈው ስልጣን የያዙት ቢሂ የምርጫውን ውጤት አከብራለሁ ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለተመራጩ ፕሬዚደንት የእንኳን ደስ ያለዎ መልዕክት አስተላልፉል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ ባወጣው አጭር መግለጫ "ተመራጩ ፕሬዚደንት እና ፕሬዚደንት ሙሴ ቢሂ መሐመድ ያሳዩትን ዲሞክራሲያዊ አመራር ኢትዮጵያ ታደንቃለች " ብሏል፡፡

የሶማሊያ ፕሬዚደንት ሀሰን ሼክ መሐሙድም ለተመራጩ ፕሬዚደንት የእንኳን ደስ ያለዎ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፕሬዚደንት መሐሙድ ለሶማሊያ ሕዝብ እድገት እና አንድነት ወሳኝ ለሆነው እርቀ ሰላም የሚደረገው ንግግር እንዲጠናቀቅ ቁርጠኛነታቸው ያሳወቁ መሆኑን የሶማሊያ መንግሥት የዜና ማሰራጫ ዘግቧል፡፡

በሶማሊያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲም በበኩሉ ምርጫውን አስመልክቶ ለሶማሊላንድ ሕዝብ እና ለተመራጩ ፕሬዚደንት እንኳን ደስ ያላችሁ በማለት መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ኤምባሲው በኤክስ ገጹ ባወጣው ጽሁፍ "የሶማሊላንድ አስደናቂ የምርጫዎች እና የሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተሞክሮ ለቀጣናው ብቻ ሳይሆን አልፎም አርአያ የሚሆን ነው" ብሏል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG