ናይሮቢ —
ከሶማሊያ ፌዴራላዊ ሬፓብሊክ ተለይታ የራስ-ገዝ አስተዳደር የመሰረተችው ሶማሌላንድ፣ ዛሬ ረቡዕ 25ኛ የነፃነት በዓሏን እያከበረች ነው።
ከሕዝቡ ሌላ የቀንድ ከብቶች፣ ግመሎች፣ አህዮችና እና አንድ አንበሳ ሳይቀር የሶማሌ-ላንዷን ቀይ፣ ነጭና አረንጓዴ ቀለማት ያሉበትን ሰንደቅ ዓላማ ተላብሰው በዓሉን በሰልፍ አድምቀው ታይተዋል።
በዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ሶማሌ-ላንድ እንደ አንድ ነፃ አገር እውቅና ባይሰጣትም፤ መሃመድ አህመድን ለመሰሉ ዜጎቿ ግን፣ የራስ-ገዝ አስተዳደር የሚለው ሐረግ ያስቆጣቸዋል። "ሶማሌ-ላንድ በትግሏ መብቷን ተቀዳጅታለች" ሲሉም ይከራከራሉ።
ሶማሌ-ላንድ፣ ከሶማልያ ጋር የ3 ዓመት የርስ በርስ ጦርነት ካካሄደች በኋላ፣ እ.አ.አ. ከ1991 ጀምሮ እራሷን "ነፃ አገር" ብላ ብትጠራም፣ ሶማልያ ለክልሉ የራስ-ገዝ አስተዳደር (Autonomy) መብት ከመስጠት ያለፈ፣ ለነፃነቷ እውቅና አትሰጥም።