በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማሊያ መንግሥት የአይኤስ መሪው በመገደሉ መደሰቱን ገለጠ


ሶማሊያ
ሶማሊያ

በሶማሊያ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ቡድን መሪ ቢላል አል ሱዳኒ በዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ኃይሎች መገደሉ መደሰቱን የሶማሊያ መንግሥት አስታወቀ፡፡

ቢላል አል ሱዳኒን የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ኃይሎች ከትናንት በስተያ ረቡዕ ሌሊት ሰሜናዊ ሶማሊያ ገጠራማ አካባቢ ውስጥ ገድለውታል፡፡

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼኽ መሐሙድ የብሄራዊ ጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ ሁሴን ሼኽ አሊ ትናንት ለቪኦኤ የሶማልኛ ክፍል በሰጡት ቃል “የአይ ኤሱ መሪ መገደል እጅግ አዎንታዊ እርምጃ በመሆኑ በደስታ ተቀብለነዋል” ብለዋል፡፡

ባሁኑ ወቅት ዋሽንግተን የሚገኙት የሶማሊያ ፕሬዚዳንታዊ አማካሪው አስከትለው “እስላማዊ መንግሥት ለሶማሊያ የአልሸባብን ያህል አደገኛ ባይሆንም ቢላል አልሱዳኒ ሶማሊያንም ለምስራቅ አፍሪካም ሥጋት የደቀነ አደገኛ አሸባሪ ነበር” ብለዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎች የእስላማዊ መንግሥት ቡድን ቀንደኛ የፋይናንስ አስተባባሪ የነበረውን ቢላል አል አል ሱዳኒን ዒላማ ባደረገው ጥቃታቸው ፑንትላንድ ውስጥ በሚገኝ ተራራማ አካባቢ ዋሻ ውስጥ ገድለውታል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እንዳስታወቀው በተወሰደው እርምጃ ሌሎች አስር አሸባሪዎችም ተገድለዋል፡፡ በጥቃቱ የተገደለ ሲቪል ሰው እንደሌለ የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስቴር ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡

ባለሥልጣናቱ እንዳሉት የዩናይትድ ስቴትስ ኃይሎቹ የፈለጉት አልሱዳኒን ሊይዙት ነበር ያ አልተሳካም፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተን ባወጡት መግለጫ “በተወሰደው ዕርምጃ የዩናይትድ ስቴትስ እና የአጋሮቿ ደህንነት እና ጸጥታ በተሻለ ይጠበቃል፡፡

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የአሜሪካውያንን ደህንነት ለመጠበቅ ያለንን ጠንካራ ቁርጠኝነትም ያንጸባርቃል” ብለዋል፡፡

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት አማካሪው በበኩላቸው ዩናይትድ ስቴትስ የወሰደችው እርምጃ ሶማሊያ ውስጥ በአልሻባብ ላይ ብቻ ሳይሆን በእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎችም ላይ ማነጣጠሯን የሚያሳይ ትልቅ እርምጃ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የማናቸውም አባሪ ቡድን መሪ ሶማሊያ ውስጥም ሆነ በአጠቃላዩ የሶማሊያ ሰላጤ አካባቢ ፈጽሞ መሸሸጊያ እንደማያገኙ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ገልጸዋል፡፡

ቢላል አል ሱዳኒን የዩናይትድ ስቴትስ የደህንነት ባለሥልጣናት ለዓመታት ሲከታተሉት ቆይተዋል፡፡ አል ሱዳኒ አይኤስ አፍሪካ ውስጥ ለሚያካሂደው እንቅስቃሴ እንዲሁም አፍጋኒስታን ውስጥ ለሚንቀሳቀሰው አይሲስ ኬ ቡድን ገንዘብ በማሰባሰብ ቁልፍ ሚና እንደነበረው የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ተናግረዋል፡፡

አል ሱዳኒን በሶማሊያ ከአልሸባብ ጋር በነበረው ሚናው የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስቴር እአአ በ2012 ማዕቀብ መዝገብ ውስጥ አስገብቶት እንደነበርም ተገልጿል፡፡

የደህንነት ተንታኞች የሶማሊያ አይኤስ መሪዎ መገደል ለቡድኑ እና በሶማሊያ ኃይሎች በስፋት ጥቃት እየተካሄደባቸው ላሉት ሌሎችም አሸባሪ ቡድኖች በሙሉ ትልቅ ጉዳት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ እና ሶማሊያ አልሻባብን በጠንካራ ትብብር እየወጉት መሆኑን የገለጹት የሶማሊያ ፕሬዚዳንታዊ አማካሪ የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ኃይል የሚሰጠን ድጋፍ አጅግ በጣም እየጠቀመን ነው” ብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG