የሶማሊያ መንግሥት፣ በዩናይትድ ስቴትስ ለሠለጠኑ ልዩ የሶማሊያ ወታደሮች የሚሰጠው ምግብ (ሬሽን)፣ ወደ ሌሎቹ የሠራዊቱ ክፍሎች እንዲዛወር መደረጉን አመነ።
የአገሪቱ መንግሥት፣ ትላንት ኀሙስ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፣ ጉዳዩን መመርመሩን ገልጾ ተጠያቂ ናቸው የተባሉ መኰንኖች ከሥራ እንደታገዱና እንደታሰሩ አስታውቋል።
የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ኀይሎች፣ በማሻሻያ መርሐ ግብሩ መሠረት፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተጠያቂነት ርምጃዎችን አጠናክሮ መቀጠሉን መግለጫው አመልክቷል።
የታገዱትንና የታሰሩትን ፖሊሶች ቁጥር እና ማንነት ግን አልገለጸም። ድርጊቱ መቼ እንደተፈጸመ የሶማሊያ መንግሥት ባይገልጽም፣ ወደፊት በሚያካሒዳቸው ምርመራዎች ዝርዝር መረጃዎችን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃድር መሐመድ ኑር፣ በጉዳዩ ላይ የሰጡት አስተያየት የለም። በሞቃዲሾ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም፣ ለአሜሪካ ድምፅ ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም።
ይኹን እንጂ መግለጫው፣ የሶማሊያ መንግሥት “በዳናብ ሬሽን ላይ በተፈጸመው ድርጊት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ለዩናይትድ ስቴትስ ይገልጻል፤” በማለት ማመኑ፣ ዋሽንግተን ድጋፏን እንደቀጠለች ፍንጭ የሰጠ ኾኗል።
የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከአልሻባብ ጋራ በሚደረገው ትግል፣ ከሶማሊያ ሕዝብ እና መንግሥት ጋራ ያለውን ስትራቴጂያዊ አጋርነት እንዲሁም ወሳኝ የሰብአዊ እና የልማት ድጋፍ እንደሚያደንቅ ገልጿል።
መድረክ / ፎረም