ሶማሊያ ውስጥ ዛሬ ረቡዕ በተፈጸሙ ሁለት በመኪና ላይ የተጠመዱ አጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃቶች ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸው ተገለጠ።
አጥፍቶ ጠፊዎቹ ዒላማ ያደረጉት የመንግሥቱ ኃይሎች መንግሥት የአልሻባብ ታጣቂዎችን እያጠቁ በሚገኙበት አካባቢ ያሉ ወታደራዊ ተቋማትን እንደነበር የሀገሪቱ ፖሊሶች አስታውቀዋል።
ጥቃቱ ንጋት ላይ የደረሰው ሂራን ክፍለ ግዛት ማሃስ ወረዳ ውስጥ ሲሆን ኦስማን አብዱላሂ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለአሶሲየትድ ፕሬስ በሰጡት ቃል ፍንዳታው በከተማው ዙሪያ ከተሰማ በኋላ ወታደሮች እና አብረዋቸው የነበሩ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን ከጥቃቱ ቦታ አውጥተናል ብለዋል።
ሁለቱ ፈንጂ የተሞሉ መኪናዎች ሲቪሎች በሚበዙበት አካባቢ መፈንዳታቸውን ነው የፖሊስ ባለስልጣኑ የገለጹት። አልሻባብ ለጥቃቱ ኅላፊ ነኝ ብሏል።