በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማሊያ መንግሥት 40 የሚሆኑ የአል- ሻባብ ታጣቂዎችን መግደሉን ገለጸ


ፎቶ ፋይል፦ የታጠቁ የአልሸባብ ተዋጊዎች ከሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ወጣ ብሎ በፒክ አፕ መኪናዎች ተቀምጠው፤ እአአ ታኅሣስ 8/2008
ፎቶ ፋይል፦ የታጠቁ የአልሸባብ ተዋጊዎች ከሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ወጣ ብሎ በፒክ አፕ መኪናዎች ተቀምጠው፤ እአአ ታኅሣስ 8/2008

የሶማሊያ መንግሥት በታችኛው ሸበሌ ክፍለ ግዛት ባካሄደው አዲስ ጥቃት አርባ የሚሆኑ የአል-ሻባብ ታጣቂዎችን ገድለናል ሲል አስታወቀ።

የሀገሪቱ የማስታወቂያ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ ብሔራዊ የጦር ሠራዊት ከ "ዓለም አቀፍ አጋሮቹ" ጋራ በመተባበር ወታደራዊ ዘመቻውን ማካሄዱን አመልክቷል።

ከዋና ከተማዋ ከሞቃዲሾ በስተሰሜን ሠላሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ የተካሄደው ጥቃት መቼ እንደተካሄደ መግለጫው ባይጠቅስም ነዋሪዎች ሰኞ ማታ መሆኑን ተናግረዋል። የመንግሥቱ መግለጫ እንዳለው እርምጃው የተወሰደው ታጣቂዎቹ በህዝብ ላይ ጥቃት ለማድረስ በአካባቢው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የሚያመለክት ጥቆማ ከደረሰ በኋላ ነው።

የአል-ሻባብ የዜና ማሰራጫዎችም ጥቃቱን የሚመለከት ዘገባ አውጥተዋል። አንደኛው የቡድኑ ድረ ገጽ ሰባት ልጆችን ጨምሮ 18 ሲቪሎችን ገድለናል ያለ ሲሆን በመንግሥቱ ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ያሏቸውን ምስሎችም የቡድኑ ሚዲያዎች አውጥተዋል።

ቪኦኤ በሁለቱም ወገኖች የቀረቡትን አሃዞች በነጻ ምንጭ ለማረጋገጥ አልቻለም።

ቱርክ እና ዩናይትድ ስቴትስ በአልሻባብ ታጣቂዎች ላይ የአየር ጥቃት የሚያካሂዱ ሲሆን በዚህ በኋለኛው ጥቃት የትኛው ዓለም አቀፍ አጋር እንደተሳተፈ የሶማሊያ መንግሥት መግለጫ በውል አልጠቀሰም። አልሻባብ ማስረጃ ሳያቀርብ ባግዳድ በተባለው መንደር የቱርክ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት አድርሰዋል ማለቱን ዘገባው አመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG