በድጋሚ የታደሰ
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሳን ሼክ መሃሙድ ከኢትዮጵያ ጋር ለአንድ ዓመት ያክል ሻክሮ የቆየውን ግንኙነታቸውን ለማደስ ስምምነት ላይ በደረሱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ፕሬዝዳንቱን በቦሌ አየር ማረፊያ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ሁለቱ መሪዎች ዛሬ ቅዳሜ ማምሻውን በሰጡት የጋራ መግለጫ ሁለቱም ሀገራት በየመዲናቸው ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና በማድረግ ግንኙነታቸውን "ወደነበረበት ለመመለስ እና ለማሻሻል" መስማማታቸውን ተናግረዋል።
መግለጫው "መሪዎቹ የቀጠናው መረጋጋት በሁለቱ ሀገራት መካከል በሚኖር ጠንካራ መተማመን፣ እና መከባበር ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግ አረጋግጠዋል" ሲል አስፍሯል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በተደረገላቸው ግብዣ መሰረት ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዙ ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።
መግለጫው አክሎም “ከኢትዮጵያ መሪ ጋር የሚደረገው ውይይት በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እና ቅድሚያ በሚሰጧቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ ላይ የሚያተኩር ነው” በማለት አስፍሯል። ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር እ.ኤ.አ በጥር 2024 የባህር በር ለማግኘት በገባችው አወዛጋቢ ስምምነት የተነሳ፤ ተጋግሎ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን በጎርጎርሳውያኑ ታህሳስ 11/ 2024 አድሰዋል።
‘የመግባቢያ ስምምነት’ በመሰኘት የሚጠራው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት፤ ኢትዮጵያ 20 ኪሎ ሜትር የባህር ጠረፍ ለ50 ዓመታት በሊዝ እንድትገለግል ሲያስችል፤ በአንጻሩ ለሶማሊላንድ ዲፕሎማሲያዊ እውቅና ለመስጠት ታስቦ እንደነበር የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የሶማሊያ መንግስት ስምምነቱን “ባዶ እና ምንም” በማለት ውድቅ ያደረገው ሲሆን ኢትዮጵያ የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ላይ "ዓይን ያወጣ ጥሰት" ፈጽማለች ሲል ከሷል።
በቱርክ ፕሬዝዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶዋን ሸምጋይነት በተካሄደው "የአንካራ መግለጫ" የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ መሪዎች አንዳቸው ለሌላው ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነፃነት እና የግዛት አንድነት ያላቸውን ክብር እና ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች የጋራ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ እና ለኢትዮጵያም አስተማማኝ እና ቀጣይነት ያለው የባህር በር አገልግሎት የምታገኝበትን የንግድ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችሏቸውን ውል፣ የሊዝ እና መሰል አደረጃጀቶችን በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
በመዲናዋ አዲስ አበባም የሶማሊያ ፕሬዝዳንትን ፎቶ በኤሌክትሮኒክስ ሰሌዳዎች ላይ በዋና ዋና አውራ ጎዳናዎች ላይ እንደተለጠፈ የአሜሪካ ድምጽ የአፍሪካ ቀንድ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ አስታውቋል።
ከፎቶዎቹ በአንዱ ስር "ፕሬዝዳንት ሼክ መሃሙድ እንኳን ደህና መጡ" የሚል ጽሁፍ ሰፍሯል።
የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማዎችም በከተማው እየተውለበለቡ ታይተዋል።
ከቦሌ አየር ማረፊያ ወደ ቤተ መንግስት የሚወስዱት መንገዶች በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥበቃ ስር ቆይተዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ዛሬ ቅዳሜ የሚያደርጉት ጉብኝት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ወደ አፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት ጉባኤ እንዳልግባ ተከልክያለሁ ካሉ በኋላ የመጀመሪያቸው ሲሆን፤ ጉብኝቱ ‘ገንቢ’ መሆኑን አንካራ አስታውቃለች።
ፕሬዝዳንት መሃሙድ ከአዲስ አበባ አስቀድሞ በካማፓላ ዩጋንዳ በግብርና ልማት ጉዳዮች ላይ ለመወያየት እና በአህጉራዊ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ተገኝተው ነበር። ፕሬዝዳንቱ በካምፓላ ከኬኒያው አቻቸው ዊልያም ሩቶ እና ከዩጋንዳው መሪ ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ተገናኝተዋል። የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ከአንካራው ስምምነት አስቀድሞ የአሸማጋይነት ሚና ነበራቸው።
የሶማሊያ መግለጫ “የፕሬዝዳንቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በቅርቡ የኤርትራ እና ጅቡቲ ውጤታማ የሆኑ ጉብኝቶችን አካል የሆነ ሰፊ ቀጠናዊ ጉብኝት ነው” በማለት አስታውቋል።
የኬኒያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሶማሊያ ባለፈው ዓመት የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ቀጣናዊውን የኢኮኖሚ ቡድን ከተቀላቀለች በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት "በፍጥነት እየተጠናከረ" ነው ሲሉ ከመሃሙድ ጋር ያደረጉትን ውይይት አስመልክተው አስተያየት ሰጥተዋል።
መድረክ / ፎረም