በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጁባላንድ ከሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ጋራ ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን አስታወቀች


በሶማሊያ ከሚገኙ ስድስት የፌዴራሉ ዓባል ግዛቶች ውስጥ አንዷ የሆነችው በደቡብ የምትገኘው ጁባላንድ
በሶማሊያ ከሚገኙ ስድስት የፌዴራሉ ዓባል ግዛቶች ውስጥ አንዷ የሆነችው በደቡብ የምትገኘው ጁባላንድ

በሶማሊያ አንድ የፌዴራሉ ዓባል የሆነ ግዛት ከማዕከላዊ መንግሥት ጋራ ያለውን ግንኙነት ማቋረጡን ተከትሎ በሃገሪቱ የሚታየው የፖለቲካ ቀውስ ተባብሷል።

በሶማሊያ ከሚገኙ ስድስት የፌዴራሉ ዓባል ግዛቶች ውስጥ አንዷ የሆነችው በደቡብ የምትገኘው ጁባላንድ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋራ ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን በይፋ አስታውቃለች፡፡

ይላል የግዛቲቱ ካቢኔ ስብሰባን ተከትሎ ዛሬ ከኪሲማዮ የወጣው መግለጫ፣ “ከሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ጋራ ያላትን የሥራ ግንኙነት ማቋረጧን ጁባላንድ ታስታውቃለች” ይላል።

ፑንትላንድም ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋራ ያላትን ግንኙነት ማቋረጧ ይታወሳል።

ጁባላንድ መነጠሏን ያስታወቀችው፣ በሞቃዲሹ የሚገኝ ፍርድ ቤት በጁባላንድ መሪ ላይ የመያዢያ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ተከትሎ ነው። መሪዉ አህመድ ሞሃመድ ኢስላም ወይም አህመድ ማዶቤ የሃገሪቱን መረጃ ለውጪ ሃገር አሳልፈው ሠጥተዋል በሚል “የሃገር ክህደት” እና ሕገ መንግስቱን የሚፃረር ተግባር በመፈጸም ክስ ቀርቦባቸዋል።

ጁባላንድ ባወጣችው መግለጫ የሶማሊያውን ፕሬዝደንት ሃሳን ሼክ ሞሃሙድ “ሥልጣንን ካለ አግባብ በመጠቀም” ከሳለች፡፡ ፍርድ ቤቱም “ገለልተኝነት ይጎድለዋል” ብላለች፡፡

ውዝግቡ የጀመረው ባለፈው ወር ሞቃዲሹ ላይ በተካሄደ ብሔራዊ የምክክር ስብሰባ ላይ ነበር። በስብሰባውም የፌዴራል መንግስት እና አንዳንድ ግዛቶች በመጪው ሰኔ 2017 የአካባቢ ምርጫ ለማካሄድ፣ በመስከረም ደግሞ የግዛቶች እና የፓርላማ ምርጫ ለማድረግ ተስማምተው ነበር።

የጁባላንዱ መሪ ግን ምርጫውን በዛ ወቅት ለማካሄድ የሥልጣን ዘመንን ማራዘም ይጠይቃል በሚል ተቃውመዋል። አህመድ ማዶቤ በጁባላንድ ባለፈው ሰኞ በግዛቲቱ ፓርላማ በድጋሚ መሪ ሆነው ተመርጠዋል። የፌዴራል መንግስት ግን ድርጊቱን በማውገዝ በድጋሚ መመረጣቸውን እውቅና እንደማይሰጥ አስታውቋል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ውጥረቱ ባየለበት ሁኔታ የፌዴራል መንግስቱ ወደ ጁባላንድ ሠራዊቱን ልኳል።

በጁባላንድ የአፍሪካ ኅብረት ኃይል አካል የሆኑ የኢትዮጵያ እና የኬንያ ወታደሮች ይገኛሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG