የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ ወታደሮች በአፍሪካ ኅብረት ልዑክ ውስጥ መካተታቸውን በተመለከተ “መልሶ ለማጤን” ዝግጁ መኾኑን አስታውቋል።
በጉዳዩ ላይ ለመናገር ፈቃድ ስላልተሰጣቸው ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉ አንድ ከፍተኛ የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣን በተለይ ለቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ እንዳስታወቁት፣ የሶማሊያ መንግሥት ለልዑኩ ኅይል ከሚያዋጡት ሀገራት ማለትም ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ጂቡቲ እና ቡሩንዲ ወታደሮችን ማግኘቷን እና መደልደሏን አስታውቀዋል።
ሁለቱ ሀገራት አንዱ የሌላውን ሉዐላዊነት፣ እንዲሁም የግዛት አንድነት እንደሚያከብር አንካራ፣ ቱርክ ላይ ባለፈው ሳምንት በፈጸሙት ስምምነት አስታውቀዋል። ስምምነቱ በመፈጸሙም ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች በአዲሱ ልዑክ ውስጥ የመካተታቸውን ጉዳይ “እንደገና እንደምታጤን” ባለሥልጣኑ ለቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ ክፍል አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋራ የፈጸመችውንና የባሕር በርን የተመለከተውን የመግባቢያ ስምምነት የማትሰርዝ ከኾነ ወታደሮቿ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ሶማሊያ ስትጠይቅ ቆይታ ነበር። ሶማሊያ ይህን ብትልም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በሶማሊያ የሚገኙት ወታደሮቹ አል ሻባብን መዋጋት እንደሚቀጥሉ ሲያስታውቅ ቆይቷል። የኢትዮጵያ ትኩረት አል ሻባብ ላይ መኾኑን የኢትዮጵያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በቅርቡ አስታውቀው ነበር።
የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላምና ጸጥታ ቡድን ባካሄደው ስብሰባ አል ሻባብ የደቀነው ስጋት እንደሚያሳስበው ገልጾ፣ በስማሊያም ኾነ በኅብረቱ ኅይሎች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት አውግዟል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ለልዑኩ የገንዘብ ምንጭ አማራጮችን እንዲያጤን የአፍሪካ ኅብረት ጠይቋል።
መድረክ / ፎረም