በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊያ "በቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት ተልእኮ ማን እንደሚሳተፍ የምወስነው እኔ ነኝ" አለች


ፎቶ ፋይል፦ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ
ፎቶ ፋይል፦ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ

የሶማሊያ መንግሥት እአአ በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ላይ በሀገሯ ሥራ እንዲጀምር ለታቀደው የአፍሪካ ኅብረት አረጋጊ ተልእኮ (አውሶም) ወታደር የሚያዋጡ ሀገሮችን እንደሚመርጥ አረጋግጧል።

የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ሶማሊያ የተልእኮውን አቅጣጫ "ትኩረቱን በግልጽ ሉዓላዊነት ላይ" ባደረገ መንገድ ትመራዋለች ብሏል፡፡

ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው ስምምነት ሉዓላዊነቴን የሚጥስ ነው ስትል ሶማሊያ ትከራከራለች።

"ከሶማሊያ ሰሜናዊ ክልል ጋር የተደረገውን ስምምነት ጨምሮ፣ ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜያት የወሰደቻቸው የተናጠል እርምጃዎች ሉዓላዊነታችንን የሚጥስ እና ለሰላም ማስከበር አስፈላጊ የሆነውን አመኔታ የሚሸረሽር ነው።" ሲል መግለጫው አመልክቷል።

መግለጫው የወጣው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ሶማሊያ ውስጥ ጦር ባላቸው አራት ሀገራት፣ ማለትም ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ጅቡቲ ያደረጉትን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ ነው። መሀሙድ ሶማሊያ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ቢኖራትም ኢትዮጵያን አልጎበኙም፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተያየቱን እንዲሰጥ ከቪኦኤ ለቀረበለት ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም።

ኢትዮጵያ የአውሶም አካል ሆና ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆኗን አመላክታለች።

ባለፈው ነሀሴ ኢትዮጵያ ወደ አዲሱ የአውሶም (AUSSOM) ተልዕኮ የሚደረገው ሽግግር “አካባቢው ላይ አደጋ ደቅኗል” ስትል አስጠንቅቃለች።

ኢትዮጵያ አዲሱን ተልዕኮ የማዘጋጀት ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት "የቀጠናውን ሀገራት እና ሠራዊት ያዋጡ ሀገራትን ተገቢ ስጋት ከግምት ማስገባት አለባቸው” በማለት አሳስባለች፡፡

ሽግግሩ እየተዘጋጀ ባለበት በዚህ ወቅት ክልሉ “ወደ ማይታወቅ አደጋ እየገባ ነው” ስትልም ኢትዮጵያ ያላትን ስጋት አመልክታለች።

“ኢትዮጵያ የጥላቻ መግለጫዎችን እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የከፈለውን መስዋእትነት ችላ መባሉን በዝምታ እንድታልፈው እየተጠበቀ ነው” ስትልም ኢትዮጵያ በመግለጫዋ አክላለች፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG