በኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ ሞሀመድ የተመራ የከፍተኛ ልዑካን ቡድን ዛሬ ሶማሊያን ጎብኝቷል። ጉብኝቱ የተደረገው ሁለቱ ሀገራት በሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሚና ዙሪያ ያለውን ያልጠራ ሁኔታ ለመፍታት እየሞከሩ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ነው።
የልዑካን ቡድኑ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ምስጋኑ አረጋ እና ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የደኅንነት ተቋማት የመጡ ባለሥልጣናትን አካቷል። በኢትዮጵያ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ ሞሀመድ የተመራ የከፍተኛ ልዑካን ቡድን ዛሬ ሶማሊያን መጎብኘቱን ያረጋገጡት የሶማሊያ የደኅንነት ባለሥልጣናት ውይይቱ፣ መተማመንን በመገንባት እና ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሊኖራት በሚችለው ሚና ዙሪያ ያተኮረ ነው ብለዋል።
የስለላ ተቋሙ ኃላፊ አብዱላሂ ሳንባሎልሼ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ መሀመድ ኦማርን ጨምሮ፣ ሶማሊያ በቅርቡ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ መላኳ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሚንስትር ጉብኝት ፣ አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ በሶማሊያ ኃላፊነቱን እየተረከበ በሚገኝበት እና የወታደር መዋጮ የሚያደርጉ ሀገራት የመጨረሻ ዝርዝር እርግጥ ባልሆነበት ወቅት የተደረገ ነው።
ሞሀመድ ኤል አሚኒ ሱፍ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ድጋፍና ማረጋጋት ተልዕኮ ኃላፊ ናቸው። አዲሱ ተልእኮ ሥራ መጀመሩን በማስመልከት በወጣው መግለጫ ላይ በሶማሊያ የረዥም ጊዜ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ በቀድሞው ተልዕኮ የተመዘገቡ ስኬቶችን አዲሱ ተልዕኮ እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።
"በተባበሩት መንግሥታት ጸጥታ ምክር ቤት ውሳኔ ቁጥር 2767 መሰረት፣ ኤዩሶም በስተመጨረሻ ከአውሮፓውያኑ ጥር 1 ቀን 2025 ዓ.ም ጀምሮ ሥራውን ጀምሯል" ሲሉ ሱፍ ተናግረዋል። ተልዕኮው ለሶማሌ የጸጥታ ኃይሎች የተግባር ድጋፍ መስጠቱን እንደሚቀጥልም አክለዋል።
የሶማሊያ ባለሥልጣናት በኤዬሶም ስር የሚሰለፉ አስፈላጊ 11 ሺሕ ወታደሮችን ከዩጋንዳ፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ማግኘታቸውን በመግለጽ ኢትዮጵያ እንደማትሳተፍ አመላክተዋል።
ከፍተኛ የሶማሊያ ባለሥልጣናት ጉዳዩ ከኢትዮጵያ ልዑካን ጋራ ውይይት እንደተደረገበት ለቪኦኤ የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት አረጋግጠዋል።
የድህረ-አትሚስ የሰራዊት ስብጥር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት ሚናን ጨምሮ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸል።
አክለውም "ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ተይዘው በነበሩ ስፍራዎች ሌሎች የጦር አጋር ሀገራት ወታደሮች መመደባቸውን ሶማሊያ ለኢትዮጵያ ወገን አስታውቃለች "ብለዋል።
“የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ሰራዊታቸውን ረዘም ላለ ጊዜ ከተንቀሳቀሰባቸው አካባቢዎች ለማዛወር ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች አጢኗል። የመጨረሻ ውሳኔ ባይሰጥም የሶማሊያ የልዑካን ቡድን በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ዝርዝር ሂደቶችን ያጠናቅቃል። ንግግሮቻችን ለጋራ መግባባት እና ትብብር ያለንን የጋራ ቁርጠኝነትን አንፀባርቀዋል። " በማለትም የውይይቱን አንኳር ጉዳይ ነው ያሉትን አስተያየት ሰጥተውናል።
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አመሻሹን ከሶማሊያ ተመልሷል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ነብያት ጌታቸውን ቪኦኤ ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም ።
የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ጸጥታ ተንታኝ ሰሚራ ጋይድ "ኤዩሶም"፣ ከቀድሞው የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ "አትሚስ" የተለየ ይሆናል ብለው እንደማይጠብቁ ይናገራሉ ።
የወታደሮቹ እና የማዘዣ ጣቢያዎች ቁጥር ከቀድሞው ያነሰ እንደሚሆን ተናግረዋል። “በመሬት ላይ ትግበራ የአሁኑ ተልዕኮ ከ"አትሚስ" ወይም ከመጨረሻዎቹ "ኤዩሶም" ቀናት የተለየ አይሆንም።የአፍሪካ ኅብረት ኃይሎች ላለፉት ስድስት ዓመታት እንበል ለውጥ አልባ እና በመከላከል ላይ ይበልጡኑ ያተኮረ ሆኗል። ውስን በሆኑት ቁጥሮች እና ማዘዣ ጣቢያች ምክንያት በተለይ አሁን ላይ ሁኔታው ይለወጣል ብዬ አላስብም።” ብለዋል።
ኤዩሶም ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የመጀመሪያ 12 ወራት የሥራ ዘመኑ ጽድቆለታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረት 1 ሺሕ 40 ፖሊሶችን ጨምሮ እስከ 12 ሺሕ 626 መለዮ ለባሾችን እስከ ሰኔ 30 ቀነ 2025 በሚዘልቀው የተልዕኮው የመጀመሪያ ምዕራፍ የሥራ ዘመን እንዲያሰማራ ሥልጣን ሰጥቶቷል።
ነገር ግን በኢትዮጵያ ወታደሮች ሚና ዙሪያ የተረጋገጠ ውሳኔ ባለመኖሩ የተፈጠረው አለመግባባት በአዲሱ ተልዕኮ ዙሪያ ስጋት አርብቧል። አንዳንድ የሶማሊያ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያን ተሳትፎ ሲጠራጠሩ ፣ሌሎች ደግሞ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋራ የተፈራረመችውን አወዛጋቢውን የመግባቢያ ስምምነት በተመለከተ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በአውሮፓዊያኑ ታኅሣሥ 11 አዲስ ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ፣ ሶማሊያ ለኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ሚና “ ክፍት ናት ” ብለዋል።
ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በሰራዊቱ ሚና ላይ ሲስማሙ ይችላሉን ? ተብለው የተጠየቁት ቀጠናዊ ተንታኟ ሰሚራ ጋይድ ሊስማሙ ይችላሉ፣የሚል ዕምነት አላቸው።
"ከአንድ ወር በፊት ሶማሊያ ካላት አቋም አንጻር በፍጹም አይሳካም እል ነበር። ነገር ግን የተጣደፈ የሚመስለው እና ሁለት ሳምንት ዕድሜ ብቻ ያለው የአንካራ ስምምነት ነገሮችን ቀይሯል። ይህ ስምምነት ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት የሚኖረውን ሚና በተመለከተ ለመወያየት ፣ መሰረት ለመጣል ታስቦ የተደረሰ ይመስላል። ሶማሊያ በኢትዮጵያ ተሳትፎ በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ መስማማት ብትችልም፣ በሕዝቡ ዘንድ ካለው ስሜት እና የሶማሊያ አመራር በጉዳዩ ላይ ከወሰደው ጠንካራ አቋም የተነሳ ከፍተኛ የፖለቲካ ዋጋ ያስከፍላል” ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል። ሰሚራ ጋይድ ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ተጨባጭ ርምጃ አልወሰዱም ብለዋል።
"ግንኙነቱን ለማሻሻል ተጨባጭ ርምጃዎች ተወስደዋል ብዬ አላምንም። ይህ የሆነው በዋናነት ምንም በይፋ የታየ ነገር ባለመኖሩ እና ጊዜውም በጣም አጭር በመሆኑ ነው።
ስምምነቱ ሁለት ሳምንት አልሞላውም። አሁንም ከሶማሊያ ፖለቲከኞች እና ፖሊሲ አውጪዎች የሚቃረኑ መግለጫዎች ይወጣሉ።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋራ በመሆን በአዲስ አበባን ከመጎብኘታቸው ፣አሁን ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ወደ ሶማሊያ ከማቅናታቸው ውጭ ፣ሌላ ነገር የለም እላለሁ "
ከአውሮፓዊያኑ 2012 ጀምሮ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ አካል ናቸው ። ኢትዮጵያ ሁለቱ ሀገራት በገቡት የቀደመ ሁለትዮሽ ስምምነት መሰረት ሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተጨማሪ ወታደሮችም አላት።
መድረክ / ፎረም