የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሃሰን ሼክ ሞሃመድ በእ.አ.አ 2022 ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ለሰባተኛ ጊዜ ወደ ኤርትራ አቅንተዋል።
ሼክ ሞሃመድ ከፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋራ ተገናኝተው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በሚጠናከርበት እንዲሁም በቀጠናዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ መንግስታዊ የሆነው የሶማሊ ብሔራዊ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ሃሰን ሼክ ሞሃመድ ባለፈው ሐምሌ ኤርትራን ጎብኝተው የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱም ሁለቱ መሪዎች “ታሪካዊ የሆነውን ግንኙነታቸውን በተመለከተ እንዲሁም በተለይም በፖለቲካዊ፣ የፀጥታ፣ በወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ መስኮች ግንኙነታቸውን በሚያሳድጉበትና የሁለቱን ሃገራት ሕዝቦች ጥቅም በሚያስጠብቁባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል” ሲሉ የኤርትራ ባለሥልታናት አስታውቀው ነበር።
ኤርትራ በርካታ የሶማሊያ ወታደሮችን ያሰለጠነች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ከእግረኛ፣ ከአየር ኃይል እና ከባህር ኃይል የተውጣጡ የሶማሊያ ወታደሮችን በማሰልጠን ላይ ነች፡፡
ሃሰን ሼክ ሞሃመድ ወደ ኤርትራ ከማቅናታቸው በፊት በአሜሪካ የሰለጠኑ ልዩ ኃይሎች ምረቃ ላይ ተገኝተዋል።
ከአፍሪካ ኅብረት ልዑክ የጸጥታ ጥበቃውን ልመረከብ ዝግጅት ላይ የምትገኘው ሶማሊያ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲና ኡጋንዳ እንዲሁም ከሌሎች ሃገራት የወታደራዊ ስልጠና እገዛ ማግኘቷ ይታወቃል።
መድረክ / ፎረም