በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊያ 3ሺህ አስተማሪዎችን ልትቀጥር ነው


ፎቶ ፋይል፡ መምህሩ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎችን እያስረማረ፤ ሞቃዲሾ፣ ሶማሊያ
ፎቶ ፋይል፡ መምህሩ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎችን እያስረማረ፤ ሞቃዲሾ፣ ሶማሊያ

የሶማሊያ ትምህርት ሚኒስቴር በጀት በአራት እጥፍ መጨመሩን ተከትሎ፣ 3ሺህ አስተማሪዎች እንደሚቀጠሩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሃሳን ሼክ ሞሃመድ ባለፈው እሁድ አስታውቀዋል። እርምጃው በአገሪቱ የሚታየውን የትምህርት ክፍተት የደፍናል ተብሏል።

ተቺዎች እንደሚሉት ግን ለትምህርት የሚመደበው ገንዘብ አሁንም በቂ አይደለም። በተጨማሪም በአገሪቱ ያለው የፀጥታ ሁኔታና ድህነት ሕጻናት ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ እንቅፋት ሆኗል ሲሉ ተቺዎቹ ይናገራሉ።

የቪኦኤው አህመድ ሞሃመድ ከሞቃዲሹ እንደዘገበው የአዲሱ የፈረንጆች ዓመት በጀት በሶማሊያ ለዓመታት ትኩረት ያልተሰጠው የትምህርት ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጓል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት ትምህርት ወደ ኋላ እንዲጎተት ምክንያት የሆነውን የአስተማሪዎች እጥረት ለመቅረፍ 3 ሺህ አስተማሪዎች ይቀጠራሉ።

ከቪኦኤ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት በሶማሊያ ትምህርት ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጄኔራል የሆኑት ሞሃመድ ሃሳን አስተማሪዎች በእጅጉ ይፈለጋሉ ብለዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም እስከሁን 1 ሺህ አስተማሪዎች ብቻ እንዳሉና ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሰው ሕጻናት ውስጥ አንድ አራተኛው ብቻ የትምህርት አቅርቦት እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

አነስተኛ የትምህርት ሥርጭት ባላቸው እናዲሁም አል-ሻባብ ለቆ በወጣባቸው አካባቢዎች ትኩረት እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል።

በአል-ሻባብ ቁጥጥር ስር ያሉ አካባቢዎች መደበኛ ትምህርት አይሰጥም። ቡድኑ እጅግ አክራሪ የሆነ የእስልና እምነትን የሚያንጸባርቅ ሥርዓተ ትምህርትን በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች ጭኗል ሲል የቪኦኤው አህመድ ሞሃመድ ዘገባ አመልክቷል።

በሶማሊያ ያለው የትምህርት ሥርጭት በዓለም ላይ ዝቅተኛ ከሚባሉት አንዱ መሆኑንና ሦስት ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ቤት ውጪ እንደሆኑ የተመድ የሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ያስታውቃል።

XS
SM
MD
LG