ሶማልያ የምግብና የውሃ እጥረት የገጠመውን፣ ከ2ሚሊዮን የሚሆነውን ህዝቧንና፣ አገሪቱን 80 ከመቶ የወረረውን ድርቅ አስመልክታ፣ የአስቸኳይ የሰብአዊ ጊዜ አውጃለች፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያወጡት የሶማልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሀመድ ሁሴን ሮቤል፣ ለአፋጣኝ እርዳታ ጥሪያቸውን እንደሚከተለው አሰምተዋል፡፡
“የንግድ ማህበረሰብ አባላትን ጨምሮ ሁሉም ሶማልያ ዜጎች፣ ለሃይማኖት መሪዎች፣ ለዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትና ለዓለም አቀፍ አጋሮች በሙሉ ድርቁ ባስከተለው ረሀብ ለተጎዱ ሰዎች በሙሉ እርዳታቸውን እንዲለግሱ ጥሪዬን አቀርባለሁ!”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁኔታው እጅግ የከፋ መሆኑን ገልጸው፣ አስቸኳይ ምላሽ እንድሚያስፈልገው ገልጸዋል፡፡
ባዲያ ሞዓሊም ኦስማን እየተባባሰ በመጣው ድርቅ ፣ከብቶቻቸውን ካጡ ከብት አርቢዎች መካከል አንዷ ናቸው፡፡
በድርቁ እጅግ ከተጎዱት ዝቅተኛው ጁባ ክልል አካባቢዎች ወደ ዶኻብሌይ ከተማ ተሰደው የመጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ የሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካዮች፣ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ወዳሉ ተረጅዎች ዘንድ ለመድረስ የሚደረገ ጥረት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ባሉ ግጭቶች የተነሳ የተፈለገውን ያህል አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡
በሞቃድሾ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰብአዊ ጉዳዮች ረዳት አስተባባሪ የሆኑት ሲንዲ አይዛክ እንዲህ ይላሉ
"እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በሶማልያ ያሉ፣ አጋር የረድኤት ድርጅቶችና ባለሥልጣናት፣ የሚሰጠውን የእርዳታ ሥራ ለማጠንከር፣ በተለይም በዋናነት፣ የውሃ አቅርቦትን በመከታተል፣ የውሃ ጉድጓዶችን በመጠገን፣ የምግብና የጤና እርዳታዎችን በማዳረስ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ግን፣ እጅግ ከፍተኛ እጥረት የሚታይበትን የውሃና የምግብ ፍላጎት ለሟሟላት፣ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት በመኖሩና እና በግጭቱ በተጎዱ አካባቢዎች ወዳሉ ተረጅዎች ዘንድ ለመድረስ ባለመቻሉ፣ ጥረቱ ከፍተኛ ችግር ገጥሞታል፡፡”
የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት የምግብ እጥረቱ እኤአ እስከ ግንቦት 2022 ድረስ ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
የሚጠበቀው ዝናብ አሁንም የማይጥል ከሆነ ብዙ ቤተሰቦች ያላቸውን ስለሚጨርሱ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ይገጥማቸውና አደጋውን መቋቋም ያቅታቸዋል ብሏል፡፡