ሶማልያ በሞቃዲሾ የሚሰሩት የኢትዮጵያ ዲፕሎማት እውቅና የላቸውም አለች፡፡ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ ዲፕሎማቱ ከዲፕሎማሲያዊ ሚናቸው ጋር የማይጣጣሙ ተግባራትን ፈጽመዋል ሲል ከሷል።
ሞቃዲሾ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካሪ የሆኑት ዲፕሎማት አሊ ሞሃመድ አዳን ትዕዛዙ በደረሳቸው 72 ሰዓታት ውስጥ ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡም ተነግሯዋል።
ሶማሊያ በአሊ ተፈጽሟል የተባለውን ድርጊት በዝርዝር ባትገልጽም፣ የሚኒስቴሩ መግለጫ ውሳኔው የተላለፈው “የቪየናን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስምምነት በመጣሳቸው” መሆኑን አመልክቷል፡፡
የአሜሪካ ድምፅ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ወዲያውኑ ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
አዲስ አበባ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ፣ ሶማሊያ ስምምነቱ ሉዓላዊነቷን የጣሰ አድርጋ በመቁጠሯ፣ ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የከረረ ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ በበኩላቸው “የባህር በር-ለእውቅና” የተባለውን የመግባቢያ ስምምነት ተገቢነት በመግለፅ ተከላክለዋል።
መድረክ / ፎረም