ሶማሊያ ውስጥ “ባንክሮፍት” ከተባለ የዩናይትድ ስቴትስ የግል የደኅንነት ኩባኒያ የሚሰሩ የታጠቁ የጥበቃ ሰዎች ዛሬ ዓርብ ጠዋት ባደረጉት እንቅስቃሴ ወቅት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን የደረሰን ዜና አስታወቀ፡፡
የታችኛው ሸበሌ ክፍለ ግዛት አስተዳዳሪ አሊ ኑር ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ግድያው የተፈፀመው ከሞቃዲሾ በስተ ደቡብ ምሥራቅ፣ ሃምሳ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለች ባሪ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ እርሻ ቦታ ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
ነጮችና ጥቂት ሶማሌዎች ያሉበት ኃይል ጥቃት አድርሶ ዘጠኝ ሰዎች ህፃናትም ጭምር ገድሏል ብለዋል።
ከተገደሉት መሃል የእርሻ ቦታ ባለቤቶችና ሠራተኞቻቸው ያሉባቸው መሆኑን አክለው ተናግረዋል። የታችኛው ሸበሌ ሀገረ ገዢው ለግድያው ተጠያቂ ያደረጉት ሶማሊያ ላሉ የአፍሪካ ኅብረት ኃይሎች የሎጅስቲክስ እና የሥልጠና ሥራ የሚሰራው “ባንክሮፍት” የተባለው ኩባኒያ የታጠቁ ሶማሌዎችና የውጭ ሰዎችን ነው።
እሳቸው እንደሚሉት ታጣቂዎቹ ስላካሄዱት እንቅስቃሴ የሶማሊያ መንግሥት መረጃ አስቀድሞ አልተሰጠውም። ግድያው በተፈፀመበት ወቅት በአካባቢው ምንም ዓይነት ውጊያ አልነበረም ያሉት ባልሥልጣኑ ታጣቂዎቹ የተሳሳተ ጥቆማ ተሰጥቷቸው ሳይሆን አይቀርም ብለዋል።
የሶማሊያ መንግሥት አሚሶም እና ባንክሮፍት አስተያየት ለማግኘት አልተቻለም።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ