በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሞቃዲሾው የአልሻባብ ጥቃት የተገደሉት ሰዎች ቁጥር አሻቅቧል


ሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ከትናንት በስተያ ቅዳሜ በደረሰው የአልሻባብ ቦምብ ፍንዳታ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ማሻቀቧል ተባለ፡፡
ሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ከትናንት በስተያ ቅዳሜ በደረሰው የአልሻባብ ቦምብ ፍንዳታ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ማሻቀቧል ተባለ፡፡

ሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ከትናንት በስተያ ቅዳሜ በደረሰው የአልሻባብ ቦምብ ፍንዳታ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 119 ማሻቀቡን ከፍተኛ የመንግሥቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡

ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ባለሥልጣን ለቪኦኤ የሶማሊኛ ክፍል በሰጡት ቃል ያሉበት ያልታወቁ ሌሎች 10 ሰዎች እንዳሉ አመልክተዋል፡፡

በመንግሥት የተሰየመው የብሄራዊ አደጋ ምላሽ ኮሚቴ በጥቃቱ የቆሰሉ 324 ሰዎች መመዝገባቸውንም ባለሥልጣኑ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ስለሁለቱ የቦምቦ ፍንዳታዎች ዝርዝር መግለጫዎችን የሰጡት ባለሥልጣኑ፣ በመጀመሪያው ፍንዳታ የደረሰው ኢላማ በተደረገው የትምህርት ሚኒስቴር ህንጻ ላይ ሲ አጥፍቶ ጠፊዎቹ በተሽከርካሪ ላይ የተጠመደ ቦምብ ማፈንዳታቸውን አስረድተዋል፡፡ ሁለተኛው ፍንዳታ ደግሞ የደረሰው በሞተር ቢስኪሌት በሚጎተት ተሳቢ ላይ በተጫኑ ቦምቦች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቅዳሜው ጥቃት እአአ ጥቅምት 14/2017 በዚያው ስፍራ ከደረሰውና 1000 ሰዎች ከተገደሉበት እና ከቆሰሉበት ጥቃት ቀጥሎ በሞቱት ሰኦው ብዛት ሁለተኛው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የአልሸባብ ሚሊሻዎች ለቅዳሜው ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰዱ ሲሆን፣ ከአምስት ዓመት በፊት ለነበረው ጥቃት ግን፣ ምንም እንኳ የአልሸባብ ታጣቂ ጥቃቱን በማቀነባበር ወንጀል የተፈረደበት ቢሆንም አልሻባብ ኃላፊነት አልወሰደም፡፡

የሶማሊያ መንግሥትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥቃቱን አውግዘዋል፡፡

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሼኽ መሃሙድ የቦምብ ጥቃቱ “በሞራል የከሰረው ወንጀለኛው የአልሻብብ ቡድን ጭካኔና ፍርሃት በተሞላበት መልኩ በንጹሃን ሰዎች ላይ የፈጸመው የሽብርተኞች ጥቃት ነው” በማለት አውግዘውታል፡፡

በዋሽንግተን የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ጄክ ሰሊቫን ዩናይትድ ስቴትስ “ይህን አሳዛኝ የሽብርተኞች ጥቃት አጥብቃ ታወግዛለች” ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው አያይዘውም “ለሶማሊያ ህዝብና የሚወዷቸውን ላጡ ወይም በሰላማዊ ሰዎች ላይ ህሊና ቢሶች ባደረሱት ጥቃት ለቆሰሉት ሁሉ “ጥልቅ ሀዘናችንን እንገልጻለን፡፡ የሶማሊያ መንግሥት ይህን መሰሉን ጭካኔ የተመላበት የሽብር ጥቃት ለመከላከል የሚያደርገውን ትግልም ለማገዝ ዩናይትድ ስቴትስ ያላትን ቁርጠኝነት ትቀጥልበታለች” ብለዋል፡፡

ከኒው ዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ በቃል አቀባያቸው ስቴፋን ዱጃሪክ በኩል ባወጡት መግለጫ በጥቃቱ “እጅግ ማዘናቸውን” ገልጸዋል፡፡

“ዋና ጸሀፊው ይህንን የጭካኔ ጥቃት በጥብቅ ያወገዙ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት እንዲህ ዓይነቱን የጽንፈኝነት ጥቃት በመቃወም ከሶማልያ መንግሥት ጋር በማበር ይቆማል” ማለታቸውን ቃል አቀባያቸው አስታውቀዋል፡፡

XS
SM
MD
LG