በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊያ ሆቴል ከበው ያጠቁት እና ሌሎች 50 የአልሸባብ ታጣቂዎች ተገደሉ


ታዛቢዎች እና የፀጥታ መኮንኖች በማዕከላዊ የሶማሌ ከተማ ቤለድዌን ከተማ በሚገኝ ሆቴል በመኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፍንዳታ ያስከተለውን ሁኔታ ይመለከታሉ፤ እአአ መጋቢት 12/2025
ታዛቢዎች እና የፀጥታ መኮንኖች በማዕከላዊ የሶማሌ ከተማ ቤለድዌን ከተማ በሚገኝ ሆቴል በመኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፍንዳታ ያስከተለውን ሁኔታ ይመለከታሉ፤ እአአ መጋቢት 12/2025

በሶማሊያ የጸጥታ ኅይሎች በማዕከላዊ ቤለድዌን ከተማ የሚገኘውን ሆቴል ከበው ያጠቁትን ስድስቱን ታጣቂዎች መግደላቸውንና በኋላም ቢያንስ 50 የአልሸባብ ታጣቂዎች የአየር ጥቃት መገደላቸውን አስታወቁ፡፡

የቤለድዌን ወረዳ ኮሚሽነር ኦማር ኦስማን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሆቴሉ ላይ የተፈጸመው የከበባ ጥቃት ዛሬ ረቡዕ ጧት ማብቃቱን አረጋግጠዋል።

ኮሚሽነሩ “የጸጥታ ኃይሎቻችን የሀገር ሽማግሌዎችና የጸጥታ ሃላፊዎች እየተገናኙ በሚመክሩበት ሆቴል ላይ ጥቃት ያደረሱ ስድስት ታጣቂዎችን በተሳካ ሁኔታ አስወግደዋል" ብለዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪነት የተፈረጀው አልሸባብ ትላንት ማክሰኞ ለደረሰው የሆቴል ጥቃት ኃላፊነቱን ወስዷል።

በአፍሪካ ኅብረት ወታደሮች የሚደገፉት የመንግሥት ወታደሮች ሆቴሉ ውስጥ በታጣቂዎቹ የተከበቡትን የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወታደራዊ መኮንኖችን እና ሰላማዊ ዜጎችን ለመታደግ ሌት ተቀን ጥረት ማድረጋቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም “በ18 ሰዓታት ከበባ ጊዜ ጀግኖች ወታደሮቻችን ሁለት ታጣቂዎችን ገድለዋል፤ ማምለጥ እንደማይችሉ የተረዱት አራቱ ተስፋ ቆርጠው በራሳቸው ላይ ቦምብ አፈንድተው ሞተዋል። የመንግሥት የጸጥታ ኃላፊዎችን እና ሁለት ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሌሎች ሰባት ሰዎች ተገድለዋል”ብለዋል፡፡

እኤአ ከነሐሴ 2022 ጀምሮ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ መሐሙድ አልሸባብ ላይ “አጠቃላይ ጦርነት” እንዲካሄድ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ፣ በሂርሸበሌ ግዛት፣ ኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ፣ ከሞቃዲሾ በስተሰሜን 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ቤለድዌን ከተማ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ አልሸባብ ላይ ለሚያካሂደው ቅስቀሳ ማዕከል ሆና ቆይታለች።

ከተማዋ ከሞቃዲሾ በስተቀር ከሌሎቹ የሶማሊያ ከተሞች የበለጠ የሽብር ጥቃት ደርሶባታል። እኤአ ከ2009 ጀምሮ በሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች እና የመንግሥት ካምፖች ላይ በተፈጸሙ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። እ.ኤ.አ. በ2009 በተፈጸመው ትልቁ ጥቃት ቢያንስ 25 ሰዎች ሲሞቱ 60 ሰዎች ቆስለዋል።

የሆቴል ከበባው ማብቃቱን ተከትሎ የሶማሊያ የጸጥታ ኅይሎች በተለያዩ የሂርሼበሌ አካባቢዎች በርካታ የአልሻባብ ታጣቂዎች መግደላቸውን የመንግሥቱ የብሔራዊ ደኅንነት እና ጸጥታ ተቋም አመልክቷል፡፡

ተቋሙ ባወጣው መግለጫ "የሶማሊያ የጦር ሠራዊት ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋራ በመተባበር በመካከለኛው ሸበሌ ክፍለ ግዛት ቢያንስ 50 የአልሻባብ ታጣቂዎችን ገድሏል፡፡ ከተገደሉት መካከልም የውጊያ ተሽከርካሪዎች አስተባባሪ የሆነ ከፍተኛ የአልሻባብ መሪ ይገኝበታል" ብሏል፡፡

መግለጫው አክሎም ዳማሻ እና ሻቢሎው የተባሉ አካባቢዎች ላይ ያነጣጠረው የአየር ጥቃት ለሽብር ጥቃት የሚሰማሩ ተሽከርካሪዎች አዘጋጅ የሆነውን ማንሱር ቲማ ዊይን የተባለ ከፍተኛ የቡድኑ መሪ ገድሎታል ሲል አስታውቋል፡፡ የሶማሊያ ወታደራዊ ዕዝ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ደግሞ" በቀጠናው የሚካሄደው ጸረ ሽብርተኛ ጥረት አካል የሆነው ርምጃ የአልሻባብን የውጊያ አቅም በእጅጉ አዳክሞታል" ብሏል፡፡

የሶማሊያው የብሔራዊ ደኅንነት ተቋም አክሎም "ከአልሻባብ ጋራ የተሳሰሩ 12 ብዙኀን መገናኛ አውታሮችን እና ድረ ገጾችን ዘግተናል" ሲል አስታውቋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG