የሶማልያው ጽንፈኛ እስላማዊ ቡድን ዐል ሸባብ ባለፈው ቅዳሜ ከሞቕድሹ እንደወጣ ይታወሳል። የሶማልያው ፕረዚዳንት ሼኽ ሸሪፍ አሕመድ አማጽያኑ መሸነፋቸውን ገልጸዋል። ዐል-ሻባባ ግን ወታደራዊ ማፈግፈግ ነው ያደረግኩት ይላል።
ስለ ጉዳዩ እንዲያብራሩልን የጋበዝናቸው የአፍሪቃ ጥናትና ምርምር ምሁር ዶክተር አለም ሃይሉ በበኩላቸው ዐል-ሻባብ ከሞቕድሾ የወጣው ተገፍቶ ነው ይላሉ። "በሶማልያ በደረሰው ረሃብ ምክንየት ሰዎች ከሀገሪቱ ለመውጣት ሲሞክሩ ስለከለከላቸው ተቃውሞ በማሳየታቸውና በሞቕድሾ ካለው የአፍሪቃ ህብረት ሰላም ጠባቂ ሃይል የሚደርስበትን ጥቃት ለመቋቋም ባለመቻሉ ነው ለመውጣት የተገደደው" ሲሉ አስረድተዋል።
ዶክተር አለም ሃይሉ አያይዘውም በሶማሊያ ዘላቂ መፍትሄ ሊገኝ የሚችለው በሀገሪቱ የሽግግር መንግስት ውስጥ ያለው ሽኩቻ ቀርቶ ሙስና ሲወገድና ሁሉን አቀፍ የሆነ አካታች መንግስት ሲኖር ነው በማለት አስገንዝበዋል።