በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማሊያ ጠ/ሚኒስትር የአፍሪካ ህብረት አምባሳደሩ ከአገር እንዲወጡ አዘዙ


ፎቶ ፋይል፦ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ልዩ ተወካዩን አምባሳደር ፍራንቼስኮ ማዴየራን
ፎቶ ፋይል፦ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ልዩ ተወካዩን አምባሳደር ፍራንቼስኮ ማዴየራን

ጠቅላይ ሚኒስትር መሀመድ ሁሴን ሮብሌ የማንቀበላቸው “ፐርሶና ኖን ግራታ" ያሏቸውን በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ልዩ ተወካዩን አምባሳደር ፍራንቼስኮ ማዴየራን በአርባ ስምንት ሰዓት ከአገር እንዲወጡ አዘዋቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ሌሊት ላይ ባወጡት መግለጫ አምባሳደሩን "በእርሳቸው ደረጃ የማይጠበቅ ተግባር ፈጽመዋል" ሲሉ ወንጅለው አህጉራዊው ህብረት ትዕዛዜን ተቀብሎ አምባሳደሩን ይጥራ ሲሉ ጠይቀዋል።

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት አብዱላሂ መሀመድ ፈርማጆ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩን እርምጃ ወዲያውኑ ውድቅ አድርገውታል። ይህም በሀገሪቱ መሪዎች መካከል ጭቅጭቁ መቀጠሉን የሚጠቁም ተደርጎ ታይቷል።

ፕሬዚዳንቱ ባወጡት መግለጫ ማዴየራ ሉዓላዊ ሀገራችንን የሚጻረር አድራጎት ፈጽመዋል የሚል ሪፖርት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴራችን አልደረሰኝም፣ እርምጃ እንዲወሰድባቸውም አላዘዝኩም ብለዋል። አምባሳደር ከሀገር እንዲወጡ ትዕዛዝ የሰጠው ክፍል እንዲህ ያለ ወሳኝ እርምጃ ብቻውን ለመውሰድ ሥልጣን ያለው አይደለም ሲሉም አክለዋል። በጉዳዩ ላይ የአምባሳደሩን አስተያየት ለማግኘት አንዳልተቻለ ዘገባው አመልክቷል።

በሶማሊያ የህብረቱ ልዩ ተወካይ ሆነው እአአ በ2015 የተሾሙት ሞዛምቢካዊው አምባሳደር ማድየራ ሶማሊያ ከሀገሯ ያባረረቻቸው የመጀመሪያ አምባሳደር አይደሉም። ሶማሊያ የእርሳቸውን ምክትል ሳይመን ሙሉንጎን ባለፈው ህዳር ወር አስወጥታቸዋለች።

እአአ በ2019 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ የነበሩትን ኒከለሰ ሄይሰምን ፕሮቶኮሉን ተላልፈው በሀገሪቱ በውስጥ ጉዳይ ገብተዋል በማለት ፐርሶና ነን ግራታ ብላ አባርራለች። ሂይሰም የተባረሩት ከዚያ በቀደመው ዓመት ባይዶዋ ላይ በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ በተከፈተው ተኩስ በተመድ የሚደገፉ ኃይሎች ተሳተፈዋል ወይ የሚል ጥያቄ ካነሱ በኋላ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ህበረቱ አምባሳደር እንዲወጡ ያዘዙት ከጥቂት ቀናት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት አሚሶምን የተካው አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ (አትሚስ) እስከአውሮፓውያን 2024 ዓመተ ድረስ ሥራውን እንዲቀጥል መስጠቱን ተከትሎ ነው።

XS
SM
MD
LG