በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ አጎራባች አካባቢዎች ላይ ከተፈፀመው ጥቃቶችና እየታዩ ካሉ ግጭቶች ጋር በተያያዙ ሁከት አዘል ጥቃቶች አወዳይ ከተማ ውስጥ ቁጥሩ የበዛ ሰው ሕይወት መጥፋቱ ተገልጿል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎም የሰፋ መፈናቀል ከጅጅጋ እና ሌሎችም የሶማሌ ክልል ከተሞች መከተሉ ተነግራል።
ከትናንት በስተያ፤ መስከረም 2/2010 ዓ.ም. አወዳይ ከተማ ውስጥ ሁከት የቀላቀለ ሰልፍ ያደረጉ ሰዎች ባደረሱት ጥቃት ሃምሣ ሰው መገደሉን የሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢድሪስ ኢስማኤል ለቪኦኤ የገለፁ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል አቻቸው አቶ አዲሱ አረጋ ግን አድራጎቱ መፈፀሙን አረጋግጠው የተገደለው ሰው ቁጥር ግን 18 መሆኑን ከመካከላቸውም 12ቱ የሶማሌ ተወላጆች ስድስቱ የኦሮሞ ጃርሶ ጎሣ አባላት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በተፈፀመው ሁኔታ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እንደሚያዝን ቃል አቀባዩ ጠቁመው ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑ በጥቃቱ ላይ ተሣትፈዋል የተባሉ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳዩ እየተጣራ መሆንን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይህንኑ የአወዳይ ጥቃት ተከትሎ ከሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂጂጋ ከ21 ሺህ በላይ ሰው ተፈናቅሎ ጭናቅሰን፣ ባቢሌና ሐረር ከተሞች ውስጥ የተጠለሉ መሆናቸውን ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮችና የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ አመልክተዋል፡፡
ስለዚህ የመፈናቀል ጉዳይ ምላሽ የሰጡት የሶማሌ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ኢድሪስ ኢስማኤል ሶማሌ ክልል ውስጥ የሌላ የማንም ብሄር ብሄረሰብ አባል የሆነ ነዋሪ አንድም አለመነካቱንና ሰዎቹ እየወጡ ያሉት በፈቃዳቸው ነው ቢሉም ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች ግን የምንፈርመው ተገድደን እንጂ መውጣት ፈልገን አይደለም ብለዋል።
እንዲያውም የልዩ ፖሊስ አባላት ቤት ለቤት እየዞሩ ትዕዛዝ እንደሰጧቸውና መጠጊያ ፍለጋ ሸሽተው በገቡባቸው የጦር ካምፖች ውስጥ ሁሉ ሳይቀር የደበደቧቸው መሆኑን፤ የተገደሉ ሁለት ሰዎችን በሸራ ጠቅልለው ሲወስዷቸው ማየታቸውን አንድ ተፈናቃይ ተናግረዋል።
አቶ ኢድሪስ በሰጡት ተጨማሪ መረጃ በአስራ አንድ የሶማሌ ወረዳዎች አካባቢዎች ውስጥ በተሠነዘሩ ጥቃቶች እስካሁን የሁለት መቶ አስራ ሦስት ሰው ህይወት መጥፋቱንና አርባ አንድ ሰው መቁሰሉን ገልጸዋል።
ጥቃቶቹን በኦሮሚያ ወረዳዎች ላይ እያደረሰ ያለው የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ነው መባሉንም አቶ ኢድሪስ አስተባብለው የኦሮሚያን ከፍተኛ አመራር አባላት የዘር ፍጅት በመምራት ወንጅለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ ይህንን ክሥ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት አቋም ነው ብለው እንደማያምኑ ጠቁመው “የራሳቸውን ጥፋት ለመሸፋፈን የሚሉት፣ ኃላፊነት የጎደለውና ከአቶ ኢድሪስ የአቅም ብቃት ማነስ የመነጨ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።
ለተጨማሪ የተያያዙትን የድምፅ ፋይሎች ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ