‘ሔር ኢሴ’ የተሰኘውና በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ የሚገኙት የሶማሌ ኢሳ ማኅበረሰብ የፍትህ ሥርዓት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ እንዲሰፈር መወሰኑ ታውቋል።
ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን የሚያሰፍን ነው የተባለው ከትውልድ ሲተላለፍ የመጣው የፍትህ ሥርዓት፣ የሥልጣን ክፍፍልን፣ ፍትህን እንዲሁም በማኅበረሰቡ ውስጥ አንድ ቡድን ወይም ግለሰብ የሚተዳደርበትን መርህና እሴት በግልጽ ያሰፈረ ነው ተብሏል።
ደንቦቹ በማኅበረሰቡ ውስጥም ኾነ ከሌሎች ማኅበረሰቦችና ዘውጌዎች ጋራ በሰላም አብሮ የመኖር መርህን የሚከተል እንደሆነ ከዩኔስኮ የተገኘው መግለጫ አመልክቷል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ መርህ ተደርጎ የሚታየውን የሴቶችና ሕፃናት መብት መከበር፣ የተፈጥሮ አካባቢን መንከባከብ፣ ሰላማዊ የግጭት መፍትሄዎችን እንዲሁም መረዳዳትን የሚያበረታታ እንደሆነ ተገልጿል።
‘ሔር ኢሴ’ በተረት፣ በምሳሌ፣ በሥነ ግጥም በሌሎችም ባሕላዊ ሥራዓቶች አማጅካይ ነት ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ እንደሆነም ታውቋል። በተጨማሪም በዘመናዊ ትምህርት፣ በውይይቶችና ሲምፖዚየሞች በብዙሃን በመገናኛ አማካይነት ወደ ትውልድ በመተላለፍ ላይ ነው።
ሥርዓቱ በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙትን የሶማሌ-ኢሳ ማኅበረሰብ ያስተሳሰረ እና ማንነታቸውን እና አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ያስቻለ እንደሆነም ተነግሯል።
የኢሣ ጎሳ ምክርቤት ቃል አቀባይ አቶ መሐመድ ሙሴ ጌሌ፣ የምዝገባ ሂደቱ ብዙ እንደተደከመበት ገልጸው በውጤቱም መደሰታቸውን ለቪኦኤ ተናግረዋል።
በምዝገባ ሂደቱ ወይዘሮ አያን አሊ ሙሴ የተባሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል የሚመሩት "ኢሣ ሄሪቴጅ" የተባለ ማኅበር ቁልፍ ሚና መጫወቱንና አቶ መሐመድ ጨምረው ገልጸዋል።
የኢሣ ጎሳ የሚኖሩባቸው የኢትዮጵያ፣ ጂቡቲና ሶማሊያ መንግሥታትም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ መሐምድ፣ ስለሔር ኢሴ የሚያትተው ሠነድም በሦስቱ ሀገራት መንግሥታት በጋራ መዘጋጀቱን ጨምረው ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም