ድሬዳዋ —
ካቢኔው ማምሻውን ባወጣው ባለ8 ነጥብ መግለጫ በ2004ዓም ሶስቱ ቀበሌዎች ማለትም ገርበኢሴ; አዳይቱና ኡንዱፎ አብዛኛው ነዋሪያቸው ሶማሌ ሆኖ እያለ ወደአፋር ክልል እንዲካለሉ በወቅቱ የነበሩ አመራሮች የወሰኑት ውሳኔ የሀገሪቱን ህጎች የጣሰ በመሆኑ ከአሁን በሁዋላ እንደማይቀበለው አስታውቋል::
የአፋር ክልል የእነኚህን ቀበሌዎች ነዋሪዎች ፍላጎት ማሟላት አልቻለም ያለው መግለጫው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የፌደራል መንግስት የነዋሪዎችን መሰረታዊ ፍላጎቶች በማሟላት ረገድ የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጠይቋል::
ሶስቱን ቀበሌዎች የሶማሌ ክልል የፀጥታ ሃይል ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር ፀጥታቸውን እንዲያስከብር ያዘዘው መግለጫው የክልሉ የፀጥታ ሃይሎች ከክልሉ ወሰን ሳይወጡ ድንበር አካባቢ ያለውን ፀጥታ እንዲያጠናክሩም አዟል::
ስለመግለጫው ያላቸውን አስተያዬት የጠቅኳቸው የአፋር ክልል የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊው አቶ አህመድ ካሎይታ ስለመግለጫም ምንም መረጃ አንደሌላቸውና ክልሉ ወደፊት አቋሙን እንደሚያሳውቅ ገልፀውልናል::
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ