ከምርጫ ቦርድ ለእጩዎች ማስመዝገቢያ የተሰጠን ጊዜ በዚህ ሰፊ ክልል ውስጥ ስራችንን ለመስራት አላስቻለንም ሲሉ ከግንቦት 15ቱ ምርጫ እራሳቸውን ያገለሉት ፓርቲዎች የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት (ሶዴኃቅ)፣ ድል ዋቢ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ድሕዴን) ዲቤና ደጊኒ ሕብረተሰብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ዲደሕዴን) ናቸው።
በአፋር ክልል ደግሞ የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) ባለፈው ሳምንት ከምርጫ እራሱን ማግለሱን ያስታወቀ ሲሆን ሰኞለት የአፋር ነጻአውጭ ግንባር ፓርቲ በምርጫው እንደማይሳተፍ አስታውቛል።
ሶማሌ ክልል
በሶማሊያ ክልል ውስጥ የምንንቀሳቀሰው የተቃዋሚ ፓርቲዎች “እኛ ብቻ ነን” ያሉት የድል ዋቢ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀ-መንበር ሼህ አባስ ሀጂ መሀመድ የምርጫ ቦርድ በሶማሊያ ክልል ለእጩዎች መመዝገቢያ የሰጠው ጊዜ 20 ቀን ብቻ ነው ብለዋል።
በመላ ሀገሪቱ የ60ቀን የጊዜ ገደብ ተሰጥቶ ሳለ እንደ ክልል አምስት አይነት ሰፊና የመገናኛ መንገዶች ለሌለበት ክልል የተሰጠው የ20 ቀን ጊዜ አናሳና ኢፍትሃዊ ነው ብለዋል።
የምርጫ ቦርድ ቃል አቀባይ አቶ ሙሀመድ አብዱራህማን በሶማሌ ክልል ፓርቲዎች ለእጩዎች ማስመዝገቢያ የተሰጣቸው ጊዜ 20 ቀናት መሆኑን አምነው፤ ከምርጫው እራሳቸውን እንዳገለሉ የሚናገሩት ፓርቲዎች የሚሰጡት መረጃ ግን የተሳሳተ ነው ብለዋል።
“አንድ ፓርቲ ቦይኮት አደረገ የሚባለው እጩዎችን አስመዝግቦና የምርጫው ሂደት ውስጥ ገብቶ ሲሳተፍ ነው። እነዚህ ሶስቱ የሶማሌ የፖለቲካ ድርጅቶች አንድም እጩ አላስመዘገቡም፤ ስለዚህ በምርጫው ሂደት አልተሳተፉም” ብለዋል አቶ ሙሀመድ አብዱራህማን።
በመላው ኢትዮጵያ 79 ህጋዊ ህልውና ያላቸው ምርጫዎች መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ሙሀመድ በ2002ቱ ምርጫ እጩዎቻቸውን አስመዝግበው የሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች ግን 63 ፓርቲዎች ብቻ ናቸው በሂደቱ የተሳተፉት ብለዋል።
የድል ዋቢ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀ-መንበር ሼህ አባስ ሀጂ መሀመድ ለቪኦኤ ሲናገሩ፤ መራጮችን ለማስመዝገብ ከምርጫ ቦርድ የተሰጠው የ20 ቀን የጊዜ ገደብ ሊያሰራቸው እንዳልቻለና በስተመጨረሻም ከምርጫው እራሳቸውን እንዲያገሉ ምክንያት መሆኑን ይጠቅሳሉ።
“ክልላቸን በጣም ሰፊና ተዘዋውሮ ለመስራት አስቸጋሪ ነው። እነሱ (ሶዴፓ-ኢህአዴግ) የመንግስት በጀት አላቸው፣ መኪና አላቸው። እኛ ግን ከኪሳችን አውጥተን ስለምንንቀሳቀስ፤ በ20 ቀናት ምንም መስራት አልቻልንም” ብለዋል ሼህ አባስ።
የ20 ቀን የጊዜ ገደቡ እንዲራዘምላቸው ሶስቱ ፓርቲዎች ለምርጫ ቦርድ መጋቢት 3ቀን 2002 በላኩት ደብዳቤ ያስታወቁ መሆናቸውንና የምርጫ ቦርድ ማስፈራሪያ አዘል ደብዳቤ ልኮ ጥያቄያቸውን ውድቅ ማድረጉን ሼክ አባስ ተናግረዋል።
አፋር ክልል
በአፋር ክልል ደግሞ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫው እራሳቸውን አግልለዋል። ባለፈው ሳምንት የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) እራሱን ማግለሱን ያስታወቀ ሲሆን ሰኞለት የአፋር ነጻአውጭ ግንባር ፓርቲ በምርጫው እንደማይሳተፍ ገልጿል።
ከዳፎ አይዳሂስ በክልሉ ዞን 5 የሰመሮቢ የምርጫ ክልል
“ትልቅ ተስፋ ነበረን በዚህ ምርጫ ላይ፤ ሆኖም የምርጫ ቦርድም ሜዳውን አላመቻቸም” ብለዋል የአፋር ነጻአውጭ ግንባር ሊቀ-መንበር ከዳፎ አይዳሂስ “በአፋር ክልል ውስጥ አምባገነን የሆነው የኢስማኤል (አሊ ሴሮ) አስተዳደር ለኛ እጩዎችም ሆነ ለፓርቲዎች እንቅስቃሴ ትክክለኛውን መንገድ ስላልከፈተ ምርጫውን ለቀን ለመውጣት ተገደናል።”
(የነዚህን ዜናዎች ዝርዝር በድምጽ ለማዳመጥ ገጹ በስተቀኝ ያምሩ)