ባለፈው ሣምንት አርብ ነሐሴ ዘጠኝ ቀን 2007 ዓ.ም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያ አሜሪካውያን መሐንዲሶችና ሳይንቲስቶች ማኅበር፣የካሪቢያን አዕምሮ ጥበቃ ማኅበር እንዲሁም የኢትዮ-ጵያ ወጣት ባለሞያዎች ማኅበር በጋራ በመኾን እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የዪናይትድ ስቴትስ የአዕምሮአዊ ፈጠራ ውጤቶችና የንግድ ምልክቶች ኤጀንሲ መሥሪያ ቤት ጋር በመተባበር አንድ ጉባኤ አዘጋጅተው ነበር፡፡
የጉባኤው ዓላማም በአሜሪካ የሚኖሩና በተለያየ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ኢትዮጵያውያንንና ከካሪቢያ አገራት ለመጡ አፍሪካውያን ስለ የአዕምሮ ንብረት ጥበቃና የፈጠራ ሥራዎቻቸው እንዴት የሕግ ከለላ ማግኘት እንደሚችል ዕውቀት እዲጨብጡ ለማድረግ ነበር፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ የተገኘችው ባልደረባችን ጽዮን ግርማ ስለ ኢትዮጵያ አሜሪካውያን መሐንዲሶችና ሳይንቲስቶች ማኅበር እንዲሁም ስለ ጉባኤው አዘጋጆቹን አነጋግራ የሚከተለውን ዘገባ ሠርታለች፡፡