ትላንት ረቡዕ በተደረገባቸው የግድያ ሙከራ በጥይት ተመትተው የቆሰሉት የስሎቫኪያ ጠቅላይ ሚንስትር ሮበርት ፊኮ ጉዳታቸው ለህይወታቸው የሚያሰጋ እንዳልሆነ የስሎቫክ መንግሥት አስታወቀ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተተኩሶባቸው የቆሰሉት ትናንት ከመንግሥታዊ ስብሰባ ሲወጡ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የሃምሳ ዘጠኝ ዓመቱ ፊኮ ባንስካ ቢስትሪካ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ሩዝቬልት ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል ተወስደው እየታከሙ ሲሆኑ ዛሬ ጠዋት ሆስፒታሉ በፖሊሶች ሲጥበቅ እንደነበር የቪዲዮ ምስሎች አሳይተዋል፡፡
አጥቂው ጠቅላይ ሚንስትሩን በአምስት ጥይት መትቶ በአስጊ ሁኒታ ያቆሰላቸው ሲሆን ወደሆስፒታሉ ተወስደው ቀዶ ጥገና ህክምና ተደርጎላቸዋል፡፡
ሀንድሎቫ በተባለችው የማዕከላዊ ስሎቫኪያ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተኮሰው የሰባ አንድ ዓመት ሰው መሆኑን የሀገሪቱ የዜና ማሰራጫዎች ተናግረዋል፡፡ የትንሺቱን ከተማ ነዋሪዎች በእጅጉ ያስደነገጠውን ጥቃት ተከትሎ ከዓለም ዙሪያ ድርጊቱን የሚያወግዙ መግለጫዎች መውጣታቸው ተዘግቧል፡፡
መድረክ / ፎረም