በኬንያ፣ ትላንት ረቡዕ፣ መንግሥትን ለመቃወም የወጡ ሰልፈኞች፣ ከፖሊስ ጋራ ተጋጭተው፣ ስድስት ሰዎች እንደተገደሉ የፖሊስ አባላት ነግረውኛል፤ ሲል፣ የኤኤፍፒ ዜና ወኪል ዘግቧል።
የታክስ ጭማሬን በመቃወም፣ በተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ የተጠራው ሰልፍ፣ “ፈቃድ አልተሰጠውም” በሚል እንዳይካሔድ ባለሥልጣናት ከልክለው እንደነበር፣ ዜና ወኪሉ ጨምሮ አስታውቋል።
ሁከቱን ተከትሎ፣ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኪቱር ኪንዲኪ፣ ከዚኽ በኋላ መንግሥት ለረብሻ ትዕግሥት አይኖረውም፤ ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ከስድስቱ ውስጥ አምስቱ የተገደሉት፣ ከመዲናዪቱ ናይሮቢ ዳርቻ ባሉ ሁለት ከተሞች ሲኾን፣ አንድ ሕይወት የጠፋው ደግሞ፣ ናይሮቢን ከወደብ ከተማዋ ሞምባሳ በሚያገናኘው አውራ ጎዳና ላይ ተቃውሞ በተደረገበት ወቅት እንደኾነ ታውቋል።
ፖሊስ፣ አስለቃሽ ጋዝ መተኮሱን ተከትሎ፣ በደርዘን የሚቆጠሩ አዳጊዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውንና አንዳንዶቹም ራሳቸውን ስተው እንደነበር ዘገባው አመልክቷል።
በኬንያ፣ መንግሥት ያወጣው የታክስ ሕግ፣ የነዳጅ ዋጋን ጭማሪ በማስከተል፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኬንያውያንን ሕይወት ይበልጥ አስቸጋሪ አድርጎታል፤ በሚል፣ የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ተከታታይ ሰልፍ እንዲደረግ ጥሪ አድርገዋል።
መድረክ / ፎረም