በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከመተማ የተፈናቀሉ እየተመለሱ ነው


መተማ ዮሃንስ ከተማ /ፎቶ - ፋይል/
መተማ ዮሃንስ ከተማ /ፎቶ - ፋይል/

“መተማን ከሌላው አካባቢ የሚለያት የሁሉም ክልሎች ማኅበረሰቦች የሚኖሩባት ሃገሪቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በብዛት የሚገኙባት መሆኗ ነው” ሲሉ የመተማ ዮሃንስ ከተማ ከንቲባ አቶ እሸቴ መልኬ ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡

ከመተማ የተፈናቀሉ እየተመለሱ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:17:25 0:00

“መተማን ከሌላው አካባቢ የሚለያት የሁሉም ክልሎች ማኅበረሰቦች የሚኖሩባት ሃገሪቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በብዛት የሚገኙባት መሆኗ ነው” ሲሉ የመተማ ዮሃንስ ከተማ ከንቲባ አቶ እሸቴ መልኬ ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡

በቅርቡ ከተማዪቱ ውስጥ የተፈፀመው ጥቃት “በዘርም በፖለቲካም ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን የተወሰኑ ወጣቶች ያደረሱት ነው” ሲሉም ከንቲባው አመልክተዋል፡፡

በደረሰው ጥቃት አምስት ሕይወት መጥፋቱና ስድስት ወይም ሰባት ሰው መቁሰሉን፤ ንብረትን አስመልክቶ በሰማንያ አራት የንግድ ድርጅቶች ላይ ጉዳት መድረሱን አቶ እሸቴ ገልፀው ረቡዕ ነኀሴ 25/2008 ዓ.ም ከዕኩለ ቀን አካባቢ አንስቶ ለሁለት ሰዓት ያህል የቆየ ጥቃትና የመከላከል ተግባር ከተከናወነ በኋላ በዕለቱ ከቀኑ አሥር ሰዓት በኋላ አንስቶ መረጋጋት መመለሱን ከንቲባው ገልፀዋል፡፡

በከተማዪቱ ነዋሪዎች መካከል በዘር ወይም በቡድን የመከፋፈልና በፀብ የመፈላለግ ሁኔታ እንዳለ የተጠየቁት አቶ እሸቴ መልኬ “በጭራሽ፤ ማኅበረሰቡንም ጉዳት የደረሰባቸውንም ስናወያይ ይሄ የብሔርም አይደለም፤ የፖለቲካም አይደለም፤ የተወሰኑ ወጣቶች ባልገባቸው ጉዳይ ላይ ተነሣስተው የፈጠሩብን ችግር ነው ነው የሚሉት” ብለዋል፡፡

በሁኔታው ተደናግጠው ሸሽተው የነበሩ ሰዎች ወደ ከተማዪቱ እየተመለሱ መሆኑንም ከንቲባው ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የተቃዋሚው አረና ትግራይ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዶም ገብረሥላሴም የከተማዪቱ ሁኔታ እየተረጋጋ መሆኑን የትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ ህወሓት ከሚሰጠው መግለጫ መረዳታቸውንና ወደ ከተማዪቱም ዛሬ፤ ዕሁድ ደውለው ይህንኑ ማረጋገጣቸውን ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡

ዝርዝር ጉዳዮችን ፓርቲያቸው እያጠና መሆኑንና ፓርቲው አባል በሆነበት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ አማካይነት መግለጫ እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ መተማ ላይ የደረሰው አደጋ በአንድ ብሔር አባላት ላይ የተቃጣ እንዳልሆነ በቅርብ ተከታትሎ ካገኘው መረጃ እንደሚያውቅ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ - መኢአድ አስታውቋል፡፡

የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል በትግራይና በአማራ ማኅበረሰቦች መካከል እንዲያ ዓይነቱ ችግር ይፈጠራል ብለው እንደማያምኑና የጎሣን ሁኔታ የሚያቀቅኑና አንድ ጥግ ለማስያዝ የሚጥሩ ሰዎች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

በአጠቃላይ የክልሉን ሁኔታ አስመልክቶ መረጋጋት መኖሩን አቶ ሙሉጌታ ጠቁመው ጎንደርን በመሣሰሉ አካባቢዎች የስልክ ግንኙነት በማጣታቸው የተጨበጠ ማስረጃ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልፀዋል፡፡

አሁን ያለው የመረጋጋት ሁኔታ ይቀጥል አይቀጥል ግን በእርግጠኝነት ለመናገር እንደማይችሉ የመኢአዱ መሪ አክለው ጠቁመዋል፡፡

ይህንኑ የክልሉን ሁኔታ አስመልክቶ የክልሉ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለቪኦኤ በሰጡት ማብራሪያ “… በአጠቃላይ በሁሉም ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ያለው የተረጋጋ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በአብዛኛው ውይይት ላይ ነው ያለው፤ በውይይቱም ሂደት በሕይወትም፣ በአካልም፣ በንብረትም ላይ የደረሱት ጉዳቶች ኅብረተሰቡንም የክልሉንም መንግሥት አሣዝነዋል፡፡” ብለዋል፡፡

ችግሩን በሰላም ለመፍታትና መረጋጋቱ ዘላቂ እንዲሁን ለማድረግ በሁሉም ደረጃዎች ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አክለው አመልክተዋል፡፡

ለተጨማሪ መረጃዎችና ቃለምልልሶች የተያያዘውን ዘገባና ተጨማሪ የድምፅ ፋይሎች ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG