በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሣን የእሳት ቃጠሎ ለማስቆም ጥረቱ ቀጥሏል


በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሣን የእሳት ቃጠሎ ለማስቆም ጥረቱ ቀጥሏል
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:49 0:00

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሣን የእሳት ቃጠሎ ለማስቆም ጥረቱ ቀጥሏል

በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኘው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የተነሣውን የእሳት ቃጠሎ ለማስቆም ጥረት እየተደረገ መኾኑን፣ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቢምረው ካሳ፣ ዛሬ ሰኞ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ ባደረጉት ቆይታ፣ ካለፈው ሳምንት ኀሙስ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፓርኩ ውስጥ የተነሣውን ቃጠሎ ለመቆጣጠር፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ርብርብ እያደረጉ መኾኑንና ከአጎራባች ቀበሌዎች ተጨማሪ ሰዎች ወደ ስፍራው መላካቸውን ገልጸዋል፡፡

እስከ አሁን በቃጠሎው የደረሰው ጉዳት በውል አልታወቀም፤ ያሉት አቶ ቢምረው፣ ከዞንና ከወረዳ የተውጣጣ ቡድን እንዲያጠና መላኩን አመልክተዋል፡፡

በአማራ ከልል በሰሜን ጎንደር ዞን ውስጥ የሚገኘውና በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ካለፈው ሳምንት ኀሙስ፣ ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ወዲህ መንሥኤው ባልታወቀ የእሳት ቃጠሎ ውስጥ መኾኑን፣ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቢምረው ካሳ፣ ዛሬ ሰኞ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

ቃጠሎውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ወንዴ፣ ቃጠሎው በፓርኩ ውስጥ "እሜት ጎጎ" ግጭ ተብሎ በሚጠራው መንደር እንደተቀሰቀሰ ጠቁመዋል፡፡ በአካባቢው ባሉ ገደላማ ቦታዎች ያለው እሳት፣ ነፋስ ሲያገኝ ዳግም እየተነሣ ቃጠሎውን ለማስቆም አዳጋች እንዳደረገው አስረድተዋል፡፡ “አሁን በርካታ የኅብረተሰብ ክፍል ርብርብ እያደረገ ይገኛል፤” ብለዋል፡፡

እስከ አሁን በቃጠሎው የደረሰው የጉዳቱ መጠን አለመታወቁን የተናገሩት አቶ ቢምረው፣ አጥኚ ቡድን ወደ ስፍራው መላኩን አስታውቀዋል፡፡

የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በአጠቃላይ 412 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆን ቦታ የሚሸፍንና በትልቅነቱ በአገሪቱ የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዝ ፓርክ ነው። በውስጡ እንደነ ዋልያ አይቤክስ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ድኩላ፣ ቀይ ቀበሮ የመሳሰሉት ብርቅዬ የዱር እንስሳትን የያዘ ነው። በተጨማሪም፣ ከ1ሺሕ200 በላይ ልዩ ልዩ የዕፀዋት ዝርያዎች እና ከ200 የሚበልጡት የአዕዋፍ ዝርያዎች መገኛ ሲኾን፣ ከእነዚህም መካከል አምስቱ በኢትዮጵያ ብቻ እንደሚገኙ፣ ከክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና ባህል ተቋም ወይም በምኅጻሩ ዩኔስኮ፣ ፓርኩ የዓለም ተፈጥሯዊ ሀብት መኾን እንዳለበት በማመን እ.ኤ.አ. በ1978 በቅርስነት መዝግቦታል፡፡

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG