በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሴራሊዮን ፓርላማ የሞት ቅጣትን የሚሰርዘውን ህግ አጸደቀ


ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዳ ቢዮ
ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዳ ቢዮ

ሴራሊዮን በአፍሪካ አህጉር የሞት ቅጣት እንዳይፈጸም በህግ የከለከለች ሃያ ሶስተኛ ሃገር ልትሆን ነው።

የሀገሪቱ የምክር ቤት አባላት የሞት ቅጣት እንዲሰረዝ እና በምትኩ ነፍስ መግደል እና የአገር ክህደት በመሳሰሉ ወንጀሎች የሚፈረድባቸው ሰዎች በዕድሜ ይፍታህ እስራት ወይም ቢያንስ በሰላሳ ዓመት እስራት እንዲቀጡ የቀረበውን ህግ ባለፈው አርብ በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል።

ሃገሪቱ በርስ በርስ ብጥብጥ ውስጥ በነበረችበት እአአ በ1998 በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተሳትፈዋል ተብለው የተከሰሱ ሃያ አራት ወታደሮች በጥይት ከተገደሉ ወዲህ ሴራሊዮን ውስጥ በሞት የተቀጣ ሰው የለም፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ከሰማኒያ በላይ ተከሳሶች የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው ወህኒ ቤት የሚገኙ ሲሆን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዳ ቢዮ ህጉን በፊርማቸው እንደሚያጸኑት ይጠበቃል።

በሰብዓዊ መብት ቡድኖች ከቅኝ አገዛዝ ዘመን ከተወረሱ የጭካኔ አድራጎቶች አንዱ ተደርጎ የሚታየውን የሞት ቅጣት በህግ የሚሰርዙት የአፍሪካ ሃገሮች ቁጥር እየጨመረ ነው።

ባለፈው ሚያዝያ የማላዊ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሞት ቅጣት ህገ መንግሥቱን ይጻረራል ብሎ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን ቻድ ባለፈው ዓመት በህግ አግዳዋለች።

በሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ቡድን በአምነስቲ ኢንተርናሺናል መሰረት ባለፈው የአውሮፓ 2020 በመላው ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሃገሮች የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው አስራ ስድስት ብቻ ሲሆኑ በቀደመው ዓመት ሃያ አምስት እንደነበሩ ገልጿል።

XS
SM
MD
LG