በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል በ2012 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ መሠረት፣ በማኅበራዊ መገናኛ ላይ "የክልሉን ከፍተኛ ባለሥልጣን ዘልፋችኋል፣ ጥላቻ ነዝታችኋል፣ እንዲሁም ሀሰተኛ መረጃ አስተላልፋችኋል" በሚል በሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተፈርዶባቸው የነበሩ ስድስት ወጣቶችን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በነፃ እንዳሰናበታቸው ጠበቃቸው ለቪኦኤ ገለፁ።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት 2016 ዓ.ም. በክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተከስሰው በሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከአንድ ዓመት ከሁለት ወር እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከ5 ሺህ እስከ 8 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ የተጣለባቸው በነወንድሙ ቶርባ መዝገብ የተዘረዘሩ ስድስት ወጣቶች ስምንት ወራት በእስር አሳልፈዋል፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሐሙስ ታህሣስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የቀረበለትን የይግባኝ አቤቱታ ከመረመረ በኋላ በነፃ እንዳሰናበታቸው ጠበቃቸው አቶ መለሰ ዮሴፍ ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ "ተከሳሾቹ የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ ሥርጭት ለመከላከል የወጣውን አዋጅ እንዳልጣሱ፤ ይልቁንም በሀገሪቱ ህገ መንግሥት አንቀፅ 29 እና በክልሉ ህገ መንግሥት አንቀፅ 28 እና 29 የተሰጠውን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውን መጠቀማቸውን ገልፆ የታችኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ ሽሮታል" ሲሉ ጠበቃቸው ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም