ዲስከቨሪ ከትናንት በስተያ ማክሰኞ ማለዳ ከወትሮ የምድር ላይ መንደሯ ከፍሎሪዳው ብሬቫርድ የኬኔዲ የጠፈር ማዕከል በቦይንግ 747 አይሮፕላን ታዝላ በዩናይትድ ስቴትስ ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲ.ሲ. ማዕከላዊው አደባባይ፣ በተወካዮች ምክር ቤቱ፣ በከተማው አዋሣኝ ፖቶማክ ወንዝ፣ በመከላከያ መሥሪያ ቤቱ ፔንታገን እና በሬገን ብሔራዊ አይሮፕላን ጣቢያ ለወትሮ ለበረራ ዝግ የሆኑ የአየር ክልሎችን ጨምሮ እያንዣበበች ስንብቷን ካጠናቀቀች በኋላ ቨርጂንያ ውስጥ በሚገኘው ዳለስ ዓለምአቀፍ አይሮፕላን ጣቢያ አርፋለች፡፡
ዲስከቨሪ በጠፈር ግዳጅ ዘመኗ 145 ሚሊየን 221 ሺህ 675 ማይልስ መብረሯን የእንቅስቃሴ መቁጠሪያ መሣሪያዋ ያስነብባል፡፡ ይህ በሜትር ልክ ሲመነዘር 238 ሚሊየን 539 ሺህ 663.33 ከሎሜትር መሆኑ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከመሬት እስከፀሐይ ያለው ርቀት ወደ 93 ሚሊየን ማይሎች መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
በዚህ ጉዞዋ ዲስከቨሪ ሌላ አንዳችም መንኩራኩር ባላከናወነው ሁኔታ ጠፈርተኞችን፣ የምርምር መሣሪያዎችን፣ ለጠፈር ጣቢያ የግንባታና የመለዋወጫ ቁሣቁስ፣ የጠፈርተኞችን ስንቅና ትጥቅ ስታመላልስ ለሦስት አሠርት ዓመታት ያህል ኖራለች፡፡
ጎልተው ከሚነገሩላት ተግባሮቿ መካከል ለብዙ የጠፈር ምርምሮች ጭለማ ጠርማሽ ግኝቶችንና በጥልቁ ሰማይ አሰሣ ውስጥ የበዙ ስኬቶችን ያስጨበጠውን ግዙፉንና ገናናውን ሃብል ቴሌስኮፕን ልክ የዛሬ 22 ዓመት ሚያዝያ 14 / 1982 ዓ.ም ወደጠፈር ይዛ መጥቃ በዚያ አኑራለች፡፡
ዲስከቨሪ ከእንግዲህ ወደ ዘለዓለማዊ መኖሪያዋ ስሚዝሶኒያን የኤሮኖቲክስና የጠፈር መካነ መዘክር ገብታለች፡፡
በማክሰኞው የዋሽንግተን ዲሲና የአካባቢው ሰማይ የስንብት በረራዋ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ሰው በምድር ላይ በውን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ በዓለም ዙሪያ በቀጥታ ይተላለፉ በነበሩ የቴሌቪዥንና የራዲዮ ሥርጭቶች እየተከታተሉ ተሰናብተዋታል፡፡ ሐሙስ ሚያዝያ 11 ቀን 2004 ዓ.ም ደግሞ በቨርጂንያው ስሚዝሶኒያን መካነ መዘክር በተካሄደው የ “እንኳን ደህና መጣሽ” ዝግጅት በብዙ መቶ የተቆጠረ ሰው በሥፍራው ተገኝቶ ለዲስከቨሪ ፍቅሩንና ክብሩን ገልጿል፡፡
ቻሌንጀርና ኮሎምቢያ የሚባሉት መንኩራኩሮች በግዳጅ ላይ ሣሉ ዓለም አፍጥጦ እያያቸው ጠፈርተኞቻቸውን እንደያዙ መቃጠላቸውና አሣዛኝ ጠባሣ ጥለው ማለፋቸው የሚታወስ ሲሆን ጡረታ የገቡት ዲስከቨሪ ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ ብላ፣ ኢንተርፕራይዝ በኒው ዮርክ፣ ኢንዴቨር በሎስ አንጀለስ፣ አትላንቲስ በፍሎሪዳ የኬኔዲ የጠፈር ማዕከል መኖሪያቸው ይገኛሉ፡፡
ዲስከቨሪን በተመለከተ የሣይንስና ሕይወት ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ሰሎሞን አባተ ከኢትዮጵያዊው ሣይንቲስትና በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የኤሮኖቲክስና የጠፈር አስተዳደር - ናሣ የመምሪያ ኃላፊ ከሆኑት ከዶክተር ብሩክ ላቀው ጋር ተወያይቶ ነበር፡፡
ዝርዝሩን ከዝግጅቱ ያዳምጡ፡፡