በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቴኔሲ ናሽቪል ትምህርት ቤት ስድስት ሰዎች በጥይት ተገደሉ


ጥቃቱ ከተመፈጸመ በኋላ ተማሪዎች ግቢው ለቀው እየወጡ
ጥቃቱ ከተመፈጸመ በኋላ ተማሪዎች ግቢው ለቀው እየወጡ

በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ቴኔሲ ክፍለ ግዛት ናሽቪል ከተማ በሚገኝ፣ ክርስቲያናዊ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ተኩስ የከፈተች አጥቂ፣ ሦስት ተማሪዎችንና ሦስት አዋቂዎችን ገድላለች። ፖሊስ፣ አጥቂዋን በጥይት ገድሏታል።

ትላንት ሰኞ፣ ግድያውን የፈጸመችው የቀድሞዋ የትምህርት ቤቱ ተማሪ፣ ኦድሪ ሄል የተባለች የ28 ዓመቷ ወጣት እንደኾነች፣ የናሽቪል ከተማ ፖሊስ አስታውቋል፡፡ አጥቂዋ፣ የትምህርት ቤቱን ሕንጻ ካርታ እና የአገባብ ዕቅዷን በዝርዝር ንድፍ አዘጋጅታ እንደነበር ፖሊስ አመልክቷል። ጥቃቱን ለምን ልትፈጽም እንደፈለገች አስቀድማ ያሰፈረችው የጽሑፍ መግለጫዋ መገኘቱን የጠቀሰው ፖሊስ፣ ምርመራ እያካሔደበት እንዳለ አስታውቋል።

አጥቂዋ፣ ቢያንስ ኹለት አውቶማቲክ ጠብመንጃዎችንና አንድ ሽጉጥ ታጥቃ ወደ ትምህርት ቤቱ ሔዳ ጥቃቱን እንደፈጸመች ፖሊስ በመረጃው ገልጿል።

ጥቃቱን፣ “እጅግ አሳዛኝ” ሲሉ የገለጹት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት፣ እንዲህ ባሉ መሣርያዎች የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚያስቆም ሕግ እንዲደነግግ ተማፅነዋል።

አጥቂዋ፣ ኹለት ኤኬ 47 ጠብመንጃዎችንና አንድ ሽጉጥ ታጥቃ ነበር፤ መባሉን የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ባይደን፣ የእርሳቸውን የአውቶማቲክ መሣሪያ ዕገዳ ሕግ ረቂቅ ምክር ቤቱ እንዲያጸድቅ ጠይቀዋል።

ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን በበኩላቸው፤ ትላንት ዋሽንግተን ውስጥ በተካሔደው የከተሞች ሊግ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ “ልጆቻችን የተሻለ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፤” ብለዋል።

እ.አ.አ በ2022 ዓመተ ምሕረት፣ በቴክሳስ ዩቫልዲ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ ታጣቂ ተኩስ ከፍቶ 21 ሰዎችን መግደሉ ይታወሳል።

ዜናው በድጋሚ ታድሷል።

XS
SM
MD
LG