የጃፓን ህዝብ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሺንዞ አቤን ዛሬ ተሰናብቷል።
አቤ ባለፈው ዐርብ ምዕራብ ጃፓን ናራ ከተማ ውስጥ በምርጫ ዘመቻ ላይ ንግግር በማድረግ ላይ ሳሉ በነፍሰ-ገዳይ ጥይት ተመትተው መውደቃቸው ይታወሳል።
የሽኝት ሥርዓቱ ዛሬ፤ ማክሰኞ በተከናወነበት ዋና ከተማዪቱ ቶኪዮ ውስጥ በሚገኝ ዞጆጂ የቡዳ ቤተ መቅደስ ደጃፍ ላይ ቁጥሩ የበዛ ኀዘንተኛ አበባና ሌላም የአክብሮት መግለጫ ይዞ ተኮልኩሏል። ብዙዎቹም አጎንብሰው እያለቀሱ ሲፀልዩ ታይተዋል።
በዞጆጂ ቤተ መቅደስ ቤተሰባቸውና የቅርብ ወዳጆቻቸው ብቻ የተገኙበት ሥነ ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ በልማዱ መሠረት አስከሬናቸው ወደሚቃጠልበት ኪሪጋያ ማዕከል በከተማዪቱ መሃል ጎዳናዎች በአጀብ ተወስዷል።
የሺንዞ አቤን አስከሬን የያዘው አውቶሞቢል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ በፓርላማውና በሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲያቸው ቢሮ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ህይወታቸውን ያሳለፉባቸው ዋና ዋና ተቋማት በሚገኙባቸው ጎዳናዎች ላይ አልፏል።
ከለቀስተኞቹ መካከል የሃምሳ ስምንት ዕመት ዕድሜአቸው ላይ መሆናቸውን የተናገሩት መምህር ኪዬኮ ኑሚ "አቤ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ ለደኅንነታችን ዋስትና ይሰማን ነበር፤ እኔ በጣም እደግፋቸው ነበር። እንደዚህ መሆኑ በጣም ያሳዝናል" ብለዋል።
ሌላው ለቀስተኛ የመንግሥት ሠራተኛ ሂዲያኪ ሱዙኪ ደግሞ "አቤ ሰው በጣም የሚያቀርቡ፣ ተጫዋችና ቀልደኛም ሰው ነበሩ። እንደሳቸው ያለ ፖለቲከኛ ጃፓን ውስጥም ይሁን ዓለም ላይ ያለ አይመስለኝም፤ በጣም እደግፋቸው ነበር ፥ ያሳዝናል" ብለዋል።
አቤን ተኩሶ በመግደል የተጠረጠረው የአርባ አንድ ዓመቱ ቴትሱያ ያማጋሚ ወዲያውኑ ተይዞ በእሥር ላይ ይገኛል።