የዓለም መሪዎች ዛሬ ማለዳ ላይ ላረፉት የቀድሞ የእሥራኤል ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ሺሞን ፔሬስ ኀዘናቸውን እየገለፁ ነው፡፡
ሺሞን ፔሬስ የእሥራኤል መንግሥት ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በመንግሥቱ ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የሥልጣን ቦታዎች አገልግለዋል፡፡
በዘጠና ሦስት ዓመት ዕድሜአቸው ያረፉት ፔሬስ ሁለት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም ፕሬዚዳንት፣ የመከላከያ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ሆነው የሠሩ ከእሥራኤል መንግሥት ፈጣሪዎችና እስከዚህ ዘመን ከዘለቁ ጥቂት መሪዎቿ አንዱ ነበሩ፡፡
ፔሬስ በተጨማሪም በእሥራኤል ሸንጎ ወይም በክኔሴቱ ውስጥ የሕዝብ እንደራሴ ሆነው ለአርባ ስምንት ዓመታት ቆይተዋል፡፡
ፔሬስ “ለእሥራኤል ሕዝብ ሉዓላዊነት ሙሉ ሕይወታቸውን የሰጡ የራዕይና አርቆ አስተዋይ ሰው ነበሩ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ናታንያሁ፡፡
ሺሞን ፔሬስ የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ ኢንቴቤ ላይ የተካሄደውን ታጋቾችን የማስለቀቅ የዘጠና ደቂቃ ድንገተኛና የተሣካ የማስለቀቅ ዘመቻ መርተዋል፡፡
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ከሰባት ሺህ በላይ ቤተ-እሥራኤል ሲወሰዱም እርሳቸው “ዘመቻ ሙሴን”ን በበላይነት ይከታተሉ ነበር፡፡
ከፍልስጥዔም አርነት ድርጅት - ፒኤልኦ መሪ ያሲር አራፋት ጋርም በኖርዌይ መሪነት ኦስሎ ላይ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ዋይት ሃውስ ተገኝተው በፕሬዚዳንት ክሊንተን ታዛቢነት ፈርመዋል፡፡
ለዚህ ተግባራቸውና ከአረቡ ዓለም ጋርም ሰላም ለመፍጠር ጥረዋል የሚባሉት ፔሬስ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ሲሆኑ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም እአአ በ2012 ዓ.ም የነፃነት ሜዳልያ አጥልቀውላቸዋል፡፡
ሺሞን ፔሬዝ እሥራኤል በኃይል በያዘችው በዌስት ባንክ የፍልስጥዔማዊያን ክልል የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሃሣብ አፍላቂና አስፈፃሚ ነበሩ፤ ከአራፋት ጋር የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ፤ ምሥራቅ ኢየሩሣሌም ዋና ከተማው የሆነ የፍልስጥዔም መንግሥት እንዲፈጠርም የወሰዱት ሃቀኛ እርምጃ አልነበረም” እየተባሉ በተቃዋሚዎቻቸው ይወቀሣሉ፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ይመልከቱ፡፡