በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን፣ ከትላንት ረቡዕ፣ የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ማቆም አድማ ላይ እንደሚገኙ፣ አስተያየታቸውን ለአሜሪካ ድምፅ የሰጡ መምህራንና የተማሪ ወላጆች ተናግረዋል፡፡
መምህራኑ፣ ለሥራ ማቆም አድማው መነሻ የኾነው፣ “ጥያቄዎቻችን ምላሽ አለማግኘታቸውና ጥቅማችንን የሚጎዳ አሠራር መጀመሩ ነው፤” ብለዋል፡፡
ለደኅንነታቸው እንደሚሰጉ በመግለጽ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን አስተያየት ሰጪዎቹ፣ አድማው ከአንደኛ እስከ ኹለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ድረስ ባሉ በርካታ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ የመማር ማስተማር ሒደቱ እንዲቋረጥና እንዲስተጓጎል ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ከሸገር ከተማ አስተዳደር 12 ክፍላተ ከተማ ውስጥ፦ ኮዬ ፈጬ፣ ገላን፣ ፉሪ፣ ሰበታ እና ለገጣፎ ለገዳዲ በርካታ መምህራን የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉባቸው ክፍላተ ከተማ ሲኾኑ፣ አድማው በከፊል የሚካሔድባቸው ክፍላተ ከተማም መኖራቸውን ከተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የሥራ ማቆም አድማው ለሦስት ቀናት እንደሚቆይ የገለጹት አስተያየታቸውን የሰጡን መምህራን፣ በእነዚኽ ቀናት ውስጥ ምላሽ ካላገኙ፣ አቤቱታቸውን በጋራ ለክልሉ ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት ለማቅረብ ወደዚያው እንደሚያመሩ ጠቁመዋል፡፡
በሥራ ማቆም አድማው ምክንያት፣ በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች፣ ከትላንት ረቡዕ ጀምሮ የመማር ማስተማር ሒደቱ መስተጓጎሉን፣ መምህራንና የተማሪ ወላጆች ተናግረዋል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የከተማ አስተዳደሩ መምህራን ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ ግርማ፣ “የሥራ ማቆም አድማ መኖሩን እናውቃለን፤ ነገር ግን ማኅበሩ ተወያይቶ ያሳለፈው ውሳኔ አይደለም፤” ከማለት ያለፈ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልኾኑም።
መድረክ / ፎረም