ፌስቡክን ጨምሮ የማህበራዊ ሚዲያ ትስስሮችን የሚያስተዳድረው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ተቋም ሜታ፣ ጸረ-ስደተኛ ይዘቶችን በተለይ በአውሮፓ የሚያስተናግድበት መንገድ ትልቅ ጥያቄ ማስነሳቱን፣ የሜታ ገለልተኛ የይዘት ተቆጣጣሪ ዛሬ ሐሙስ አስታውቋል።
እ.አ.አ በ2020 በሜታ የተቋቋመው እና አንዳንዴ የተቋሙ "ጠቅላይ ፍርድ ቤት" ተብሎ የሚጠራው ተቆጣጣሪ ቦርድ በሜታ ላይ ምርመራ የጀመረው፣ ፀረ-ስደተኛ ይዘት ባላቸው መረጃዎች ዙሪያ "ከፍተኛ ቁጥር" ያለው አቤቱታ ከደርሰው በኃላ ነው።
ቦርዱ ሜታ የሰብዓዊ መብት ህግን እና እራሱ በጥላቻ ንግግሮች ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ እየተገበረ መሆኑን ለመገምገም፣ ከጀርመን እና ከፖላንድ የተመረጡ ሁለት ይዘቶችን መርምሯል።
የቀድሞ የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የቦርዱ ተባባሪ ሊቀመንበር የሆኑት ሄሌ ቶርኒንግ -ሽሚት "ከመላው አውሮፓ ከስደት ጋር በተያያዙ ይዘቶች ላይየሚደርሱን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አቤቱታዎች ተቋሙ ከዚህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንዴት እንደሚያስተናግድ አጥብቀን መጠየቅ እንዳለብን ያሳየናል" ብለዋል።
ቦርዱ የገመገመው የመጀመሪያ ይዘት፣ የፖላንድ ቀኝ አክራሪ ኮንፌዴሬሽን ፓርቲ በግንቦት ወር በፌስቡክ ገፅ ላይ ያጋራው የፎቶ ምስል ሲሆን፣ ምስሉ የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ በቀዳዳ እያዩ ከጀርባቸው አንድ ጥቁር ግለሰብ ወደ እሳቸው ሲጠጋ ያሳያል። ከምስሉ ጋር አብሮ መንግሥታቸው የስደተኛ ቁጥር እንዲጨምር እንደሚፈቅድ የሚገልፅ ፅሁፍ ተጋርቷል።
ሜታ፣ ጽሁፉ አንድን ዘር የሚዘልፍ መሆኑን በመግለፅ ይዘቱን እንዲያጠፋ የቀረበለትን ጥያቄ አልተቀበለውም።
በሌላ የጀርመን ፌስቡክ ገፅ ሰው ሰራሽ ልህቀትን በመጠቀም የተሰራጨ ምስልም፣ አንዲት ወርቃማ ፀጉር እና የዓይኖቿ ቀለም ሰማያዊ የሆነች ሴት የጀርመንን ባንዲራ እና “አቁም” የሚል ምልክት ይዛ የሚያሳይ ሲሆን አብሮት የተጋራው የፅሁፍ መልዕክት ስደተኞችን "የቡድን አስገድዶ ደፋሪ ባለሞያዎች" ሲል ይገልጻል። ፌስቡክ ይህንን መረጃ ከገፁ እንዲያጠፋ ጥያቄ ቢቀርብለትም ላለማንሳት ውሳኔ አሳልፏል።
ቦርዱ በምርመራው ዙሪያ ውሳኔውን ይፋ ከማድረጉ በፊት ከህዝቡ መስማት እንደሚፈልግ ገልጾ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውይይት እንደሚያካሂድ አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም