በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሴኔት ሪፐብሊካን ከትረምፕ በተቃራኒ የድንበር በጀቱን ለማጽደቅ እየገፉ ነው


የሴኔቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ ጃን ቱን
የሴኔቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ ጃን ቱን

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ በአሜሪካ የሕግ አውጪው ሸንጎ (ሴኔት) ያሉ ሪፐብሊካን አባላት በስደተኞች፣ ኃይል እና መከላከያ ላይ ያተኮረውን የበጀት ረቂቃቸውን ወደ ጎን ብለው፣ ከተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርበውን ሰፋ ያለ የበጀት ሐሳብ እንዲቀበሉ ቢጠይቁም፣ የሴኔቱ የሪፐብሊካን አባላት ግን በያዙት ሐሳብ እንደሚገፉበት አስታውቀዋል።

ትረምፕ በተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውንና በትሪሊየን ዶላር የሚቆጠር የታክስ እፎይታ ጭምር የሚሰጠውን ሰፋ ያለ የበጀት ሐሳብ እንደሚመርጡ ቢያስታውቁም፣ በሴኔቱ የሚገኙ የሪፐብሊካን አባላት ግን በያዙት አቋም እንደሚገፉ በሴኔቱ አብዛኛ መቀመጫ የያዘው የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ ጃን ቱን አስታውቀዋል።

በሴኔቱ የቀረበው “ቀጠን ያለ” የበጀት ሐሳብ፣ ትረምፕ ያሰቡትን የታክስ ቅነሳ ለመተግበር፣ ወደፊት ሌላ በጀት በምክር ቤቱ ለማጽደቅ በሚሞክሩበት ጊዜ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት በምክር ቤቱ የሪፐብሊካን አባላት ዘንድ አድሯል። ምክንያቱ ደግሞ ፓርቲው በጠባብ ልዩነት፣ ማለትም 218 ለ215 መቀመጫዎች ብቻ የበላይነት የያዘ ስለሆነና ከሁለት ዓመታት በኋላ የም/ቤት አባላት ምርጫ ሲካሄድ የበላይነቱን ሊያጡ ይችላሉ በሚል ስጋት ነው።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፣ ሁለቱም የሕግ አውጪ ም/ቤቶች “አንድ ትልቅ ሸጋ በጀት ረቂቅ” አጽድቀው በሃገሪቱ የዕርቅ ሂደቱን እንዲጀምሩ ጥሪ አድርገዋል።

ከምክትል ፕሬዝደንት ጄዲ ቫንስ እና ከሴኔት ሪፐብሊካን ጓዶቻቸው ጋራ ስብሰባ ያደረጎት የሴኔቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ ጃን ቱን፣ “ቀጠን ባለው” የበጀት ረቂቅ እንደሚገፉበት አስታውቀዋል።

“በስተመጨረሻ አንድም ሆነ ሁለት የበጀት ረቂቅ አውጥተን ፕሬዝደንቱ ያሰቡትን ከዳር እናደርሳለን” ያሉት ጃን ቱን፣ ሴኔቱ ዛሬ ሐሙስ ድምጽ ይሰጣል ብለው እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል።

ትረምፕ የተቃውሞ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ተከትሎ፣ አንዳንድ የሪፐብሊካን ዓባላት በየትኛው መንገድ መቀጠል እንዳለባቸው ግራ ተጋብተዋል ሲል የሮይተርስ ሪፖርት አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዲሞክራቶቹ ለረጅም ትግል እንደተዘጋጁ አስታውቀዋል። “የበጀት ረቂቁ የፕሬዝደንቱ ወዳጅ ለሆኑ ቢሊየነሮች የታክስ እፎይታ ለመስጠት ያለመ ነው” ሲሉ የሴኔት ዲሞክራቶች መሪው ቻክ ሹመር ክስ አሰምተዋል።

ሴኔቱ ባቀረበው የበጀት ረቂቅ ውስጥ፣ ለአራት ዓመታ የ340 ቢሊዮን ዶላር፣ በየዓመቱ 85 ቢሊዮን ዶላር ድንበር ጥበቃውን ለማጥበቅና የትረምፕን ፍልሰተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት፣ የኅይል ፖሊሲን ለመቀየር እንዲሁም የመከላከያ ወጪን ለመጨመር የሚል ተካቷል።

በተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው በጀት ደግሞ፣ 4.5 ትሪሊየን የታክስ ቅነሳና፣ 2 ትሪሊየን ዶላር የወጪ ቅነሳ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት እንዲሁም ለኃይል የፖሊሲ ልውጦች የሚውል ገንዘብን ታሳቢ ያደርጋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG